አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በኢምፕሮቬት የጋራ መድረክ የስፔስ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና አቅም ላይ አቋማን ገለጸች።
የስፔስ ቴክኖሎጂ ጥቅምን በሚመለከት በእስራኤል በተዘጋጀው የበይነ መረብ ስብሰባ ኢትዮጵያ በዘርፉ ሰለምታደርገው የተጠናከረ እንቅስቃሴ ገለጻ አቅርባለች።
ኢምፕሮቬት ባለሃብቶች፥ የፈጠራ ባለቤቶች፥ ኩባንያዎችን እና የመንግስታት የሥራ ኃላፊዎችን በሚያወያይበት ዓመታዊ የጋራ የስፔስ ኮንፈረንስ ከሀገራችን የስፔስ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ እንዲሁም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
መድረኩ “ኮሙዩኒኬሽን አፍሪካ 2021፤ ሀገር አቀፍ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማቅረብ መቻል” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ነው የተካሄደው።
በኮንፈረንሱ ከሀገር አቀፍ የኮሙዩኒኬሽን አቅም አንጻር አፍሪካ የሚያስፈልጓትን ቴክኖሎጂዎች፣ የሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን ጠቀሜታና አስፈላጊነትን፣ የኢኮኖሚ ፋይዳ፣ የአተገባበር ፍጥነቱን፣ በአጠቃላይ የሳተላይት ኮሚዩኒኬሽን የሚያስገኛቸውን መጠነ ሰፊ መፍትሄዎች ላይ ከአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ዓለም አቀፍ ኢጀንሲዎች ጋር ተመክሯል።
በኮንፈረንሱ የእስራኤል እና የአፍሪካ ሀገራት የኮሙዩኒኬሽን፣ ስፔስ እና ቴክኖሎጂ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትሮች እንደዚሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ቼንጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚስተር ቶኒ ብሌር የመክፈቻ ንግግር አቅርበዋል።
በዚህ መድረክ የስፔስ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ኢትዮጵያ በእንጦጦ ተራራ ስፔስ ሳይንስ ኦብዘርባቶሪ ማቋቋሟ፣ የስፔስ ጥናት ተቋም መመስረቷ፣ የሳተላይት እና ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ፖሊሲ ማውጣቷ፣ ሁለት ሳተላይቶችን ማምጠቋ፣ እንደዚሁም ለዘርፉ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረጓ በስፔስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ትኩረት ከሳቡ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በቀዳሚነት እንድትታይ ያደረጋት መሆኑን አስረድተዋል።
በማያያዝም ተቋሙ በሕዋ ሳይንስ መሪ መሆኑን፥ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት በማፋጠን፥ በግብርና፥ በትምህርት፥ በጤና ዘርፍ አገልግሎት የሚስጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በተቋሙ በኩል አቅም ለመገንባት በተለይ በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ አስትሮኖሚ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ጠቅሰው፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራም መጀመሩን ገልጸዋል ።
አምባሳደር ረታ መንግስት የሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን አስፈላጊነትን በመገንዘብ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት የሰጠው መሆኑን፣ በዚህ ረገድ ያሉትን ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በመግለጽ በተለያዩ ደረጃዎች በሚደርጉ የትብብር ማዕቀፎች የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በአገራችን የሕዋ/ጠፈር ሳይንስ የአቅም ግንባታ በተለይ የሰው ኃይል እና የመሰረተ ልማት ለማጠናከር መንግሥት በርካታ ተግባራት ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል ።
ኢትዮጵያ በዚህ ኮንፈረንስ በተለይም በከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ መሳተፏ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ ለቴክኖሎጂ እና ዲጂታላይዜሽን የተሰጠው ትኩረት፣ በዚህ ረገድ ትብብርን ለማጠናከርና ኢንቨስትመንት ለመሳብ እድል የሚፈጥር መሆኑን ማስገንዘብ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አስታውቋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

