አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የህወሓት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጪሊሞ ጫካ ስልጠና ላይ የነበሩ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጁንታውን ለማገዝ ወደ ትግራይ መጓዛቸውን በተሃድሶ ስልጠና ላይ የሚገኙ ወጣቶች ተናገሩ።
ከህወሓት የጥፋት ቡድን ጎን ተሰልፎ የነበረውና አሁን በደቡብ ዕዝ የማሰልጠኛ ማዕከል የተሃድሶ ስልጠና እየወሰደ የሚገኘው ወጣት ዕድሜው ከ20ዎቹ መጀመሪያ አይዘልም።
ወጣት ፈይሳ ተካ ግንደበረት አካባቢ ተወልዶ ማደጉን፤ ከአንድ ዓመት በፊት በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በአባልነት መመልመሉንና ለስድስት ወራት ገደማ በጪሊሞ ጫካ ወታደራዊ ስልጠና መውሰዱን ይናገራል።
የህወሓት ቡድን ጦርነት መክፈቱ በተነገረበት ሰሞን 26 አባላት ካካተተው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ጋር ‘ነጻ መሬትና በቂ ሬሽን ለማግኘት’ በሚል ወደ ትግራይ እንዲሄዱ እንደተነገራቸው ገልጿል።
በኋላም ‘የኦሮሚያ ልዩ ኃይል’ የሚል መታወቂያ ተሰጥቷቸው ወደ ደቡብ ትግራይ ራያ ግንባር መጓዛቸውን ተናግሯል።
በራያ ግንባር ‘ብሶበር’ በሚባል ስፍራ ከጁንታው ታጣቂ ኃይል ጋር በመሆን ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ውጊያ መግጠማቸውንም እንዲሁ።
በዚሁ ግንባር የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከትግራይ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ሲቪሎችም ተሰልፈው መዋጋታቸውን ወጣት ፈይሳ ተናግሯል።
ጦርነቱ እየጠነከረ በመሔዱ የጁንታው ታጣቂዎች ሲያፈገፍጉና ሲበታተኑ ፈይሳን ጨምሮ የተቀሩት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችም መበታተናቸውን ገልጿል።
በራያ ግንባር የመከላከያ ሰራዊት ጠንካራ እርምጃ ወስዶ አካባቢውን ሲያስለቅቅ ሁሉም መበታተናቸውንና አብረውት የነበሩትም የት እንደሆኑ እንዳማያውቅ ነው የተናገረው።
ፋይሳ ነፍሱን ለማዳን ብቻውን ረዥም ርቀት በእግሩ ሲጓዝ በመከላከያ ሠራዊት እጅ መግባቱን አስረድቷል።
በመከላከያ ከተያዘ በኋላ በመሆኒ፣ ቆቦና አላማጣ አካባቢዎች ሰራዊቱ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እያደረገለት ሲጠብቀውና ሲንከባከበው መቆየቱንም እንደተናገረ ኢዜአ ዘግቧል።
ወጣት ፈይሳ ከህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር ተሰልፈው ከነበሩ 764 ከሚደርሱ የጁንታው ታጣቂዎች ጋር የተሃድሶ ስልጠና እየወሰደ መሆኑንም ገልጿል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

