Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን እሴት ጨምሮ ማልማት የሚያስችል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና  ስርዓት ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ኢትዮጵያ ያላትን የእንስሳት ሃብት እሴት ጨምሮ ማልማት የሚያስችል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከሁሉም ክልል እና ከተማ መስተዳድር ከተውጣጡ የቴክኒካል ቮኬሽናል ትምህርት ስልጠና ቢሮ ሃላፊዎች፣ የክልል እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና  ኤጀንሲዎች፣ የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ጋር በአዳማ ተወያይቷል፡፡

በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማብሰር ከሚችሉ ዘርፎች መካከል አንዱ የቆዳ ኢንዱስትሪ መሆኑን የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ  ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ብዛት በዓለም ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሆኗን ያነሱት አቶ ጌታቸው፣ ይሁን እንጂ ይህን ጥሬ ሃብት በአግባቡ ስራ ላይ አለመዋሉን ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም  ይህንን  ሃብት እሴት ጨምሮ  በማምረት ራሱንና ሀገሩን መጥቀም የሚችል የተማረ የሰው ሃይል በሁሉም ክልል በበቂ ሁኔታ ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ቴክኖሎጂ ትምህርትና ሥልጠና በክልሎች ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው  በበኩላቸው የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን እሴት ጨምሮ ማልማት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ  በተለያዩ ክልሎች በመተግበርና በማስተዋወቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በቆዳው ዘርፍ ስልጠና ለሚሰጡ ቴክኒካል ቮኬሽናል ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ እና ለዚህም  የቴክኒክና ሙያ ስልጠና  ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version