አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ማዕድን ፈቃድ አውጥተው ወደ ስራ ሳይገቡ ከ10 አመት በላይ በሆናቸው ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል፡፡
የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር የምክር ቤት እና የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የአካበቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን በመዲናዋ በግንባታ ማዕድን ማምረቻ ቦታዎች ዙሪያ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ገምግመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የማዕድን ፍቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ ፀጋዬ የጥናቱን ውጤት በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት ሪፖርት አቅርበዋል::
ባቀረቡት ሪፖርትም በመዲናዋ በግንባታ ማዕድን ማምረት ዘርፍ ከሚሰሩ 372 ድርጅቶች ውስጥ 114ቱ ብቻ የግንባታ አሰራር ስርዓትን ተከትለው የሚሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በግንባታ ማዕድን ማምረቻ ቦታዎች ላይ የሰራተኛውን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግብአቶችን ከማሟላት አኳያ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው ጠቅሰው፤ ህገወጥ የማዕድን አምራቾችን እና አዳዲስ የማዕድን ማምረቻ ቦታዎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡
በዚህም የግንባታ ማዕድን ፍቃድ አውጥተው ከአስር አመት በላይ የሆናቸውን የማጣራት ስራ ተሰርቶ ወደ ስራ ሳይገቡ በቆዩት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ተጠቁሟል።
በተጨማሪ ፍቃድ ወስደው በሥራ ላይ የሚገኙና ወደስራ ያልገቡ ባለፍቃዶችን በመስክ መለየትና መረጃ የማጣራት ስራ የተሰራ ሲሆን፤ በጥናቱ የፍቃድ እድሳት ኖሯቸው ወደ ስራ ያልገቡ፣ እድሳት ያልፈፀሙ ብሎም ከፈቃዳቸው ውጪ ለሌላ ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች መለየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከተሰጣቸው መሬት አልፈው ይዞታ አስፋፍተው የተገኙ 7 ድርጅቶች እንዲሁም ፈቃድ ሳይኖራቸው ማምረት የጀመሩ 19 ድርጅቶችንና ግለሰቦችን መለየት እንደተቻለ ተነግሯል፡፡
የግንባታ ማዕድን ማምረቻ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ተግባራዊ አድርገው በማይሰሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ ሀይሉ ገልፀዋል፡፡
ማዕድን ተመርቶ የተጠናቀቀባቸውና እየተመረተባቸው ባሉ በማዕድን ማምረት የተጎዱ ቦታዎች የመልሶ ማልማት የተከናወነባቸውና ያልተከናወነባቸውና ቦታዎች መረጃ የማደራጀት ስራ መሰራቱን እንዲሁም በትሥሥር ከማዕድን ባለፍቃዶች ጋር እየሰሩ የሚገኙ ወጣቶች አጠቃላይ መረጃ የማደራጀት እና ሌሎች ከዘርፉ ጋር የተያያዙ በርካታ ስራዎች በጥናቱ መካተታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ 82 ድርጅቶች፣ ፍቃድ ያላሳደሱ 54 ድርጅቶች እና ውል ያቋረጡ 48 ድርጅቶች መኖራቸውንም አቶ ሀይሉ ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ዘመናዊ የአሰራር ስርአት በመዘርጋትና የማእድን አቅርቦቱን በማሳለጥ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥናቱ እንደሚረዳም ተነግሯል።
ጥናቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችን፣ ባለይዞታዎችን፣ በማምረቻ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን እና ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ መከናወኑ ተገልጿል፡፡
የምክር ቤቱ እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት በቀረበው ዳሰሳ ጥናት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን የማዕድን እና የግንባታ ዘርፉ ከዚህ በፊት በርካታ የአሰራር ችግሮች የነበሩበት እና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ እንደነበረ አውስተዋል፡፡
አሁን ላይ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ለውጥ እያሳየ እንዳለ እና የዳሰሳ ጥናት መደረጉ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ተስፋየ ተረፈ መናገራቸውን ኮሚሽኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላኩት መግለጫ አስታውቋል ።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

