አዲስ አበባ ፣ጥር 25 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመከላከያ ሰራዊቱን ስም ሲያጠለሽ የነበረና የሀገርን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚጥል የጥላቻና የሃሰት መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጭ የነበረው ግለሰብ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
ሌሎች ከሀገር ሊወጡ የነበሩና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ጭምር መያዛቸውን ተነግሯል።
‘ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጄ አበባው ታደሰን ጨምሮ ጄኔራል መኮንኖችንና ከፍተኛ የጦር አዛዦች በትግራይ ልዩ ሃይል ተገድለዋል’ የሚልና ሌሎችንም የሀሰት መረጃ “የትግራይ ልዩ ሃይል ድል” በሚል ፍሪደም ቲቪ በተባለ የዩቲዩብ አድራሻ በተለያ ጊዜ ያልተጨበጠ መረጃ ያሰራጭ ነበረ ተብሏል።
ግለሰቡ ከአዲስ አበባ በመነሳት ኬንያ ከዛም ወደ ኡጋንዳ ካምፓላ ለመውጣት ሲሞክር ሃዋሳ ላይ በደቡብ ዕዝ የሰራዊት አባላት በቁጥጥር ስር መዋሉን ኦፕሬሽኑን የመሩት ሌተናል ኮለኔል ግርማ አየለ ተናግረዋል።
ስራውን እንዲሰራ የቀጠረው እንግሊዝ ሀገር የሚኖረው ዳዊት አብርሃ ዘረዝጊ የተባለ ሰው መሆኑንና ለአገልግሎቱም 600 የአሜሪካ ዶላር ይከፍለው እንደነበር ግለሰቡ አብራርቷል።
የሚያሰራጨውን የሃሰት መረጃም እንግሊዝ ሀገር ሆኖ ዩቲዩብን ከሚያስተዳድረው ዳዊት አብርሃ እንደሚሰጠውና እሱም በውጭ ካሉ አፍራሽ እንቅስቃሴ ካላቸው ከተለያዩ የቴሌቪዝን ጣቢያዎችና ከግለሰቦች ማህበራዊ ገፅ የሚያገኘውን ያልተጣራ መረጃ አሰሪውን በማስፈቀድ ይጠቀም እንደነበርም ገልጿል።
ይህንን ስራ ከአመት በፊት እንደ ጀመረ የሚናገረው ግለሰቡ፣ መንግስት በትግራይ የህግ ማስከበር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ያልተጨበጠ የበሬ ወለደ መረጃ ማሰራጨት እንደጀመረና “እየቆየሁ ስሄድም እየሰራሁት ያለው ወንጀል የደህንነት ስጋት ላይ ስለጣለኝ፣ ከሀገር ለመውጣት ስንቀሳቀስ ነው በመከላከያ በቁጥጥር ስር የዋልኩት” ሲል መናገሩን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ደቡብ ዕዝ የሃሰት መረጃ ሲያሰራጭ የነበረውን ግለሰብ ጨምሮ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ 8 ሰዎችን እና 4 በህገ ወጥ ዝውውሩ ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን ለፌዴራል ፖሊስ ማስረከቡን ኦፕሬሽኑን የመሩት ሌተናል ኮለኔል ግርማ አየለ አረጋግጠዋል ፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

