Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት 110 የእሳት አደጋዎች ደርሰዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ 110 የእሳት አደጋዎች መድረሳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በአደጋውም የአምስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡

ከደረሱት አደጋዎች መካከል 24ቱ በንግድ ተቋማትና በልዩ ልዩ ድርጅቶች የደረሱ ናቸው ተብሏል፡፡

የኤሌክትሪክ መስመሮችን በአግባቡ አለመዘርጋት እና የኤሌክትሪክ ኃይልን በጥንቃቄ አለመጠቀም፣ በቀላሉ በእሳት ሊቀጣጠሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችንና ተቀጣጣይ ነገሮች እሳት በቀላሉ በሚያገኛቸው ቦታዎች ማስቀመጥ፣ የቡታጋዝ እንዲሁም የሲሊንደር ፍንዳታዎች የቃጠሎው መንስኤ መሆናቸውን በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጡን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የአብዛኞቹ የአደጋዎች መንስኤዎች በቸልተኝነት ያጋጠሙ መሆኑን በተለይ ደግሞ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ሻማ ለኮሶ መርሳት እንዲሁም ሰዎች በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መሳሪያዎችን ሲጠቀሙ ቆይተው በድንገት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ሳያጠፉ ባሉበት ጥሎ በመሄድ የኤሌክትሪ ኃይል ሲመጣ እቃዎቹ ግለው የእሳት አደጋ እንዲከሰት ምክንያት እንደሆኑ በምርመራው ውጤት ተረጋግጧል፡፡

በቅርቡ በኮልፌ እፎይታ የገበያ ማእከል እና  በጉለሌ የዕፅዋት ማእከልም የእሳት አደጋ ማጋጠሙ ይታወቃል፡፡

የንግድ ማእከሉ የአደጋ መንስኤ እየተጠራ እንደሆነና በጉለሌ የዕፅዋት ማእከል የደረሰውን አደጋን በተመለከተ  ዛፍ ቆርጦ ለማስጫን ጨረታ ያሸነፈው ግለሰብ ስራውን እንዲሰሩለት የቀጠራቸው ሰራተኞች ምግብ ለማዘጋጀት ባቀጣጠሉት እሳት አደጋው መድረሱን በታክቲክ ምርመራ መረጋገጡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version