Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሀይል በዞኑ የተከናወነውን የፀጥታና ሕግ ማስከበር ስራ እየገመገመ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሀይል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ የተከናወነውን የፀጥታና ሕግ የማስከበር ስራ ላይ ግምገማ እያካሄደ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተቋቋመው የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሃይል የዞኑን የፀጥታና ሕግ ማስከበር ስራ ከተረከበ በኋላ አካባቢው ወደቀድሞ ሠላማዊ ሁኔታ መመለስ ጀምሯል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ተስፋዬ ቤልጅጌና የኮማንድ ፖስቱ የጸጥታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ መድረኩን እየመሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ከዞን እስከ ቀበሌ የተዋቀረው ግብረ ሃይል በአንድ ወር ውስጥ ያከናወናቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውይይት እየተካሄደባቸው ነው፡፡

ግብረ ሃይሉ በትኩረት የሚሰራባቸው ለተፈናቃዮች ሠብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ፣ ሽፍታውን ለሕግ ማቅረብና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥን የተመለከቱ ቁልፍ ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

ግብረ ሃይሉ በወሰደው ሕግ የማስከበር ወታደራዊ ዘመቻ 50 ቀበሌዎችን ከሽፍታ ነፃ በማድረግ አካባቢዎቹን የሠላም ቀጣና ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለዓመታት ታስረው የነበሩ 837 ሰዎች ከ27 ህፃናት ልጆቻቸው ጋር ከእስር መለቀቃቸው ተጠቅሷል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በ33 ቀበሌዎች ከ16 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ሰብል መሰብሰብ እንደተቻለም ተነግሯል።

በሌላ በኩል በ61 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የነበረ የ15 ሺህ 113 ሰዎች ሰብል መውደሙ በግምገማው ተጠቅሷል፡፡

በዞኑ 98 የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውና 81 ደግሞ ወደ አገልግሎት ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸው ተገልጿል ፡፡

የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ 91 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ሲሆኑ 181 እስካሁን አለመከፈታቸው ተመልክቷል፡፡

ግብረ ሃይሉ 72 የግብርና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ስራ ቢገቡም 107 ይቀራሉ ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version