Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በስደተኞች ጉዳይ ላይ አዳዲስ መመሪያዎችን አሳለፉ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በስደተኞች ጉዳይ ላይ አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ በመፈረም ያሳለፉት ውሳኔ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሲሰራበት የቆየውን ህግ የሚሽር ነው ተብሏል፡፡

በዚህም ከወላጆቻቸው የተለዩ ስደተኛ ህጻናትን የሚመለከተውን የስደተኞች ፖሊሲ ዋነኛው መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

ከዚህ ቀደም ትራምፕ አስተዳደር በሜክሲኮ ድንበር በህገ ወጥ መልኩ ወደ አሜሪካ ገብተዋል የተባሉ ሰነድ አልባ ስደተኞች ልጆችን ከወላጆቻቸው የሚነጥል ውሳኔ አሳልፈው ነበር፡፡

አሁን ላይም ባይደን ይህን የሚሽር ውሳኔ ያሳለፉ ሲሆን፥ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ሃይልም አቋቁመዋል፡፡

የተቋቋመው ግብረ ሃይልም ከወላጆቻቸው የተነጠሉ ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት የሚችሉበትን አግባብ እንደሚያፈላልግ ተገልጿል፡፡

ግብረ ሃይሉ በሃገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትሩ አሌሃንድሮ ማዮርካስ የሚመራ ሲሆን ለጉዳዩ እልባት ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በዚህ ሂደትም በትራምፕ አስተዳደር ከወላጆቻቸው የተነጠሉ ከ600 እስከ 700 የሚሆኑ ህጻናት ጉዳይ እልባት እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባለፈም ባይደን ከስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂወች እና ለውጭ ሃገራት ከሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ አዲስ መመሪያ አሳልፈዋል፡፡

በትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች እና ጥገኝት ጠያቂዎች የሚያቀርቡት ማመልከቻ የሚታይበት ሂደት የተንዛዛና በአብዛኛውም መልካም ምላሽ የማያገኝ እንደነበር ይነገራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ለውጭ ሃገራት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ መቀነሳቸውም የሚታወስ ነው፡፡

የአሁኑ የባይደን ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ መሰል ውሳኔዎችን በመቀልበስ ለማስተካከል የሚረዳ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version