Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጎንደር ከተማ ያቋቋመውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ሥራ አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጎንደር ከተማ ያቋቋመውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ሥራ አስጀምሯል።

ማዕከሉ በጎንደር ከተማ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከልን ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን÷ ከ90 በላይ ተገበያዮችን በአንድ የግብይት መርሐ ግብር ማስተናገድ የሚችል ነው ተብሏል።

በስነስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ማዕከሉ የአካባቢው ተገበያዮች ወደ አዲስ አበባ መሔድ ሳይጠበቅባቸው በቀጥታ የግብይት ውድድሩ አካል እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ሲሆን÷ ይህም ከፍተኛ ወጪንና እንግልትን የሚቀንስ አሰራር ነው ተብሏል።

ምርት ገበያው የጥራጥሬና ቅባት እህሎችንና ቡና አቅራቢዎች ከሸማቾች ጋር በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት በመደራደር የሚገበያዩበት ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር መሆኑን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የንግድ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ስፔሻሊስት አቶ ቸርነት ታመነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአንድ ጊዜ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚይዙ ከ60 በላይ መጋዘኖችና 23 ቅርንጫፎች ሲኖሩት ከሦስት ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው።

በዚህም 12 የግብርና ምርቶችን ያገበያያል ከ17 ባንኮች ጋር በአጋርነት የሚሰራ ሲሆን÷በዓመት ከ700 ሺህ ቶን በላይ ምርት ሲያገበያይ በዓመት ከ33 ቢሊየን ብር በላይ ክፍያና ርክክብ ይፈፅማል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 347 አባላት እና ከ140 በላይ አባል ያልሆኑ ተገበያዮች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳ፣ በሑመራና በነቀምት ከ22 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት አብመድ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version