አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “አኖፌለስ ስቴፈንሳይ” የተሰኘች የወባ አስተላላፊ ትንኝ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች መገኘቷን በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት የተካሄደ ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት፣ በዩ.ኤስ.አይ.ዲ ቪክቶርሊንክ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ በኔዘርላንድስ ሬድቦድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከልና በብሪታኒያ የለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲስን ትብብር የተካሄደ ነው።
የትንኝ ዝርያዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምስራቅ የዓረብ ልሳነ-ምድር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች መገኘቷም በጥናቱ ተመላክቷል።
ትንኟ በጂቡቲ፣ በሱዳንና በሶማሊያ የተገኘች ሲሆን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2008 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ መገኘቷ ይታወሳል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ገነቱ እንዳሉት፤ ትንኟ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በምስራቅ ኦሮሚያና ምስራቅ አማራ በሚገኙ 10 ከተሞች መገኘቷ በዳሰሳ ጥናት የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ባልተከሰተችባቸው የሰሜን ምስራቅ የሃገሪቷ ከተሞች እየተስፋፋች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በውሃ ገንዳዎች፣ በብሎኬት ማምረቻ አካባቢ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች፣ ባለቀ የመኪና ጎማ ውስጥ በሚቀመጥ ውሃ፣ እርጥበት ባላቸውና ውሃ ባቆሩ አካባቢዎች ትንኟ በቀላሉ እንደምትራባም ነው የተገለጸው።
በኢንስቲቲዩቱ የወባና ትኩረት የሚሹ የቆላማና ሐሩር በሽታዎች ምርምር ዳይሬክተሩ ዶክተር እንዳላማው ጋይሳ ትንኟን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ስለ ባህሪዋና ሌሎች ጉዳዮች የመረጃ ልውውጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪም “ለመንግስት አካላት መረጃ ማድረስና ማስረዳት፣ ከጎረቤት ሃገራት ጋር መረጃ መለዋወጥ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል።
“ትንኟን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የመነሻና የስርጭት ሁኔታዋን ለማወቅ ተከታታይ ጥናት ማካሄድና ለመራቢያ ምቹ አካባቢ እንዳታገኝ ማድረግ ይገባል” ያሉት ደግሞ በዩ.ኤስ.አይ.ዲ ቪክቶርሊንክ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶክተር መሸሻ ባልከው ናቸው።
ትንኟን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለጤና ባለሙያዎችና ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርት መስጠት እንደሚያሻም ጠቁመዋል።
የምስራቅ አማራ አንዳንድ ከተሞችን ጨምሮ በሶማሌ ክልል ኤረር፣ ጂግጂጋ፣ ቀብሪደሃርና ጎዴ፣ በአፋር ክልል ሰመራ፣ ገዋኔና አዋሽ፣ በኦሮሚያ መተሃራ፣ ዝዋይ፣ መቂና ሞጆ ከተሞች እንዲሁም በድሬዳዋ ትንኟ መገኘቷን ጥናቱ ማመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

