አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪው ሀገራዊ ምርጫ ተመሳሳይ ፖሊሲ እና ፕሮግራም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት በመፍጠር ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ እንዳለባቸው የፖለቲካል ሳይንሰ ምሁራን ተናግረዋል፡፡
የፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛት እውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መፍጠር አያስችልም ያሉት ምሁራኑ ጥምረት መፍጠር ህብረተሰቡ የሚበጀውን በትክክል እንዲመርጥ ከማስቻሉ ባለፈ የሀገር ሃብትን ከብክነት ይከላከላል ብለዋል፡፡
ጥምረቱ የታሰበለትን አላማ ይመታ ዘንድም በጥናት ላይ ተመስርቶ መከወን እናዳለበት ነው ምሁራኑ የገለጹት፡፡
ይህም ተመሳሳይ ፖሊሲ እና ፕሮግራም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅንጅት ከመወዳደር ይልቅ በተናጠል ወደ ሜዳው የሚገቡበት ሁኔታ አንዱ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር ዶክተር በዕውቀቱ ድረስ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ጠንካራ እና ገዢውን ፓርቲ የሚገዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጥረት አንዱ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በርካታ ናቸው የሚሉት ዶክተር በዕውቀቱ፣ ይሁን እንጂ ፖሊሲያቸው እና ፕሮግማቸው ግን ተቀራራቢ መሆኑን ይናገራሉ ይህም ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በድርድር የመፍታት ፍላጎት አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስለሆነም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገሩቱ የፖለቲካ ስርዓት ላይ ጠንካራ መሰረት ለመጣል ካሰቡ ተሰባስበው ጥምረት መፍጠር እንዳለባቸው ነው የሚገልጹት፡፡
የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አቶ አንተነህ ተስፋሁን በበኩላቸቸው፣ ምርጫ ፓርቲዎች ተፎካካሪ እና በሀሳብ በልጠው እንዲገኙ እድል የሚፈጥር መድረክ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሂደቱን በስኬት ለማጠናቀቅም ጥምረት መፍጠር እንዳዳለባቸው ነው የሚያነሱት፡፡
ይህም ሰፊ ማህበራዊ መሰረት እና የፖሊሲ አማራጭ ያላቸው እንዲሁም ቢያሸንፉ ያለ ምንም መናወጥ ሀገርን ማስተዳደር የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መፍጠር ያስችላል ይላሉ፡፡
ለዚህም በመሰረታዊነት በሀገሪቱ ሁኔታ የሚስማሙ እና ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ ፓርቲዎች ጥምረት መፍጠር አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ዶክተር በዕውቀቱም በአቶ አንተነህ ሃሳብ ይስማማሉ፣ እሳቸው እንደሚሉት ጥምረት በምርጫ ወቅት ፓርቲዎች፣ የመራጮቻቸው ድምፅ እንዳይከፋፈል እና የተሻለ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆኖ ለመዝለቅ እና መንግስት ለመመስረት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ማህበረሰቡ የሚበጀውን ፖሊሲ በቀላሉ እንዲለይ ከማስቻሉ በላይ የሀገር ሃብት እንዳይባክን ያደረጋል ይላሉ፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎች ጥምረት በሚፈጥሩበት ወቅት አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ እስከ ታች ድረስ ያሉ አባሎቻቸው ሂደቱን ሊያምኑበት እንደሚገባ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ፡፡
ይህም በቀጣይ ያለውን አብሮነት በዘላቂነት ከማጠናከሩ ባሻገር ግልጸኝነትን ይፈጥራል ነው የሚሉት፡፡
የሚፈጠረው ጥምረት በመተማመን ላይ የተመሰረተ እና ዘላቂ እንዲሆንም በጥናት መመስረት እንዳለበት ነው ዶክተር በዕውቀቱ የሚናገሩት፡፡
ከዚህ ባለፈም ጥምረቱ የግጭት አፈታት መመሪያዎችን ማዘጋጀት እና አለመግባባቶችን ለማህበረሰቡ ይፋ ከማድረግ ይልቅ በውይይት መፍታት እና ሚስጥርን መጠበቅ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ እና ገዢው ፓርቲም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥምረት በመፍጠር ተወዳዳሪ እና ጠንካራ ሆነው እንደሚመጡ የሚያስችል ምህዳር መፍጠር እንዳለባቸው ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

