አዲስ አበባ ፣ ጥር 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተዘጋጀው የክቡር ዶ/ር አርቲስት ዓሊ ቢራ የምስጋና እና እውቅና ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
ፕሮግራሙ አርቲስቱ ለኦሮሚያ እና ለኢትዮጵያ ጥበብ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እውቅና ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
በዚህም ፕሮግራም ላይ ለክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ልዩ የኒሻን ሽልማት ተበርክቶለታል።
ከዚያም ባለፈ አርቲስቱ ለኢትዮጵያ ያበረከተው አስተዋጽኦ እና የግል ታሪኩ ላይ ያጠነጠነው በአማርኛ፣ በኦሮሚኛና በእንግሊዘኛ የተጻፈ መጽሐፍ ተመርቋል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፣የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ፣የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄነራል ይልማ መርዳሳ ፣ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌን ጨምሮ ሌሎች ፌዴራል እና የክልል መንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የጥበቡ ማኅበረሰብ፣ ቤተሰቦች፣ ጓደኞቹ እና አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።
ክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከ60 ዓመታት በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ጥበብ ፣ ባሕል እና ቋንቋ እድገት ጉልህ ሚና ያበረከተ ታላቅ ሊቅ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ዝግጅቱ አርቲስቱ ለህዝቦች ሁለንተናዊ እኩልነት እና አብሮነት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እውቅና ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
አርቲስት አሊ ቢራ በተለያዩ ቋንቋዎች በሚያቀነቅናቸው ዘፈኖቹ ኢትዮጵያዊነትን፣ወንድማማችነትን ፣አንድነትን እና አብሮነት ሲሰብክ የኖረ ድንቅ አርቲስት ነው ብለዋል።
የአርቲስቱ ስራም በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ እየታሰበ እንደሚኖር የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሽልማቱ ለሌሎች የሙያ አጋሮቹ ማነቃቂያ ይሆናል ብለዋል።
ለዚህም በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ያለኝን ክብርና አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ ነው ያሉት።
በዚህም የክልሉ መንግስት በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ የአሊ ቢራ ታሪክና ስራ የሚታይበት ክፍል እንዲኖር መወሰኑን ተናግረዋል።
አርቲስት አሊ ቢራ የሰራው ስራ ዕውቅና አግኝቶ በመሸለሙ መደሰቱን ገልጾ ምስጋና አቅርቧል።
አርቲስት አሊ ቢራ በአፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ፣ በሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣ ሐረሪ ፣ አረብኛ እና በሌሎች ቋንቋዎችም ሙዚቃን ሲጫወት ኖሯል፡፡
አርቲስቱ በተስረቅራቂ ድምፁ ዘመን ተሸጋሪ ጥዑም ሙዚቃን ከመጫወት በተጨማሪ የግጥምና ዜማ ደራሲም መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለ

