አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ በተለያዩ ከተሞች ተካሄደ፡፡
በወላይታ ዞን ሁሉም ወረዳዎችና ከሶዶ ከተማ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገሳተፉበት የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል፡፡
የሰልፉ አላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለሰጧቸው ጠንካራ አመራር በልማትና በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በዲፕሎማሲ ስራዎቻቸው ላስመዘገቡት ድሎች ምስጋና ለማቅረብና በቀጣይ ህዝቡ ከጎናቸው መሆኑን ለመግለፅ ነው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የሚያደናቅፉ የውስጥና የውጭ ሀይሎችን እናወግዛለን፣ አደናጋሪ አጀንዳዎችን በማክሸፍ የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን፣ ታላቁ የለውጥ ጉዟችን በጠቅላይ ሚኒስተሩ መሪነት ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉ መፈክሮች በሰልፉ ተሰምተዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድርያስ ጌታ ሀገሪቷ ወደተረጋጋ ሰላምና አንድነት በመደመር እሴት እንድትገባ ታላቅ የመሪነት ጥበብ ተጠቅመው የለውጥ ሂደቱን እየመሩ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲሄድ ከጎናቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሰልፉም የተለያዩ ልማታዊ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የወላይታ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የተጀመረውን ለውጥ ህዝቡ ማስቀጠል አለበትም ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ህብረተሰቡ በሃገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን የለውጥ ተግባር የሚያደንቁ ሃሳቦች አንፀባርቋል።
የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ከመንግስትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።
በጉልበትና በሀይል ስልጣን ለማግኘትና ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ ቡድኖችን አውግዘዋል።
በተመሳሳይ የድጋፍ ሰልፉ በጂንካ ከተማ እና በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማም ተካሄዷል፡፡
በጂንካ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በጁንታዉ መቃብር ላይ ብልፅግና፣ ሰላምና የሕዝቦች አንድነት ይለመልማል፤ ህብረ-ብሔራዊነትን በማጠናከር አሃዳዊነትን እንቀብራለን ” የሚሉ መፈክሮችን ሰልፈኞቹ አሰምተዋል፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ሰልፉ ሲደረግ የህዝቦችንና የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታን ሊያደፈርሱ ከሚሯሯጡ የጁንታ ተላላኪዎች ህዝቡ እራሱንና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅም መልዕክት ተላልፏል።
በተመሳሳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአጋርነትና የድጋፍ ሰልፍ በጎፋ ዞን፣ ሳውላ ከተማና በየም ልዩ ወረዳ ሳጃ ከተማ ተካሄዷል፡፡
የድጋፍ ሰልፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለሰጡት ጠንካራና በሳል አመራር፣ በልማትና መልካም አስተዳደር እየተመዘገበ ላለው ስኬት ህዝባዊ እውቅናና ድጋፍ ለመስጠት እና በቀጣይ ከጎናቸው መሆናቸውን ለመግለፅ ያለመ መሆኑን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህ ወቅትም “የጁንታውን ቡድን ለማምከን የሠጡትን በሳል አመራር እናደንቃለን፤ በእርሶ የሚመራው መንግስት የጀመረው የለውጥ ጉዞ ከግብ እንዲደርስ የበኩላችንን እንወጣለን እና አደናጋሪ አሉባልታዎችን በማክሸፍ ለለውጡ ዘላቂነት እንተጋለን” የሚሉ መልዕክቶችን ሰልፈኞቹ አስተላልፈዋል።
በኢየሩሳሌማ ደምሴና በኢብራሂም ባዲ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

