Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር “የአይኬር ኢኒሼቲቭ” ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር የሆስፒታሎችን አሠራር ለማዘመን የተቀረፀው “የአይኬር ኢኒሼቲቭ” ማስጀመሪያ ፕሮግራም መካሄዱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

“አይኬር” ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሆስፒታሎች ለማምጣት፣ ታካሚ ተኮር አገልግሎቶችን ለማጠናከር፣ በተቋም ውስጥና ውጭ ያሉ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በሆስፒታሎች አገልግሎት ዙሪያ ተግዳሮቶችን በመፈተሽ ውጤታማ አሰራሮች ለመዘርጋት የተቀረፀ ነው።

ፕሮግራሙን ለማስጀመር በቅድመ እቅድ ዝግጅት ሂደት ወቅት ባለድርሻ አካላትን በመለየት የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ፍላጎት እና ከሆስፒታሉ የሚጠብቋቸውን ውጤቶች በመዳሰስ እንደ መነሻ እንዲወሰዱ መደረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

በዕቅድ ዝግጅት ሂደቱ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የችግር ልየታ እና አፈታት ዘዴ መከናወኑን ተናግረዋል።

ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ግቦች፣ የግቡ ማሰፈጸሚያ ስልቶች፣ መለኪያዎች፣ የሚጠበቁ ውጤቶችን እና ፈጻሚ አካላትን በመለየት ግልጽ የድርጊት መርሐ-ግብር መቀመጡንም አስረድተዋል።

በመርሐ-ግብሩ ከሜዲካል ሴንተሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር በሚታዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት መደረጉንም ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።
“በተጨማሪም በሜዲካል ሴንተሩ ውስጥ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች የጤና ሚኒስቴር፣ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሜዲካል ሴንተሩ እና ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ በጋራ በመሆን መፍታት የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት ተደርጓል” ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር በዚህ ዓመት አይኬርን ለማስጀመር ከ24 ሆስፒታሎች ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version