አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ምክትል አስተዳዳሪ እና የአፍሪካ ቀጠና ሃላፊ አሁና ኢዚኮኖዋ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው ወቅትም በትግራይ ክልል ስላለው የሰብአዊ እርዳታ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ እና በድርጅቱ መካከል ስላለው ትብብር እና በመጭው ሃገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ መክረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመድ የልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ የ2030 ዘለቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለምታደርገው ጥረት የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
አያይዘውም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምና ኮቪድ19 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም መንግስት አሁን ላይ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ለተጎዱ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ፣ መልሶ ማቋቋምና በህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም መንግስት በትግራይ ክልል 92 የእርዳታ ማሰራጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም ከተመድ እና ሌሎች ረጂ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ምክትል አስተዳዳሪ እና የአፍሪካ ቀጠና ሃላፊ አሁና ኢዚኮኖዋ በበኩላቸው ከመጭው ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ድርጅቱ ተአማኒ፣ አካታች እና ሰላማዊ ምርጫ እንዲደረግ የቦርዱን አቅም ለማጠናከር የጀመረውን ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
የተመድ የልማት ድርጅት ለኢትዮጵያ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ምክትል አስተዳዳሪ እና የአፍሪካ ቀጠና ሃላፊ አሁና ኢዚኮኖዋ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን፥ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈም በመቐለ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

