አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተሠጠ ያለው የአፋን ኦሮሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ዜጎች በቋንቋቸው እንዲማሩ ዕድል የፈጠረ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡
ዶክተር አለሙ ስሜ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በክልሉ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ትምህርት ከሚሰጥባቸው ውስጥ በአሶሳ ከተማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የትምህርት አሰጣጡን ጎብኝተዋል፡፡
ዶክተር ዓለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት ÷ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአፋን ኦሮሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተሠጠ ያለው ትምህርት ዜጎች በቋንቋቸው የመማር መብታቸውን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርቱ ዜጎች በቋንቋቸው እንዲማሩ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ ብዝኃነትን በተግባር የማስተናገድ አንዱ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ እንዲማሩ ማድረግ የሚማሩትን ትምህርት በአግባቡ እንዲረዱት እንደሚያስችል የተናገሩት አቶ ዓለሙ ÷ ህብረ-ብሔራዊነት በሚስተናገድባት ሀገር ውስጥ ክልሎች መሠል ሥራዎችን ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ክልሎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር ዕድልን ከመፍጠር ባለፈ አንዱ የሌላውን ቋንቋ እንዲለምድና እንዲጠቀምበት የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ነው ያሉት ፡፡
የአሶሳ ከተማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር አቶ ያለው አድነው በበኩላቸው÷ የአፋን አሮሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት በ2012 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸው÷ በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ110 በላይ የ1ኛ የ2ኛ ክፍል ተማሪዎች በቋንቋው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በበኩላቸው አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ የመማር ዕድል ማግኘታቸው ትምህርቱን ሳይቸገሩ እንዲረዱት እያስቻለቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ20 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በአፋን ኦሮሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እየተሠጠ መሆኑ ን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

