አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኤድዋርድ ዞሊሳ ማካያ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪከ አምባሳደር ኤድዋርድ ዞሊሳ የተመራው የልዑካን ቡድን፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ተወያይቷል።
ኢትዮጵያ የአፓርታይድ ስርዓት ከደቡብ አፍሪከ እንዲጠፋ ቁልፉን ሚና ከተጨወቱት ሀገራት በግንባርቀደምትነት የምትጠቀስ መሆኗን አስታውሰው ይህም ታሪካዊ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚሁም ደቡብ አፍሪካ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በጸጥታው ዘርፍ የተለያዩ የትብብር ስምምነት ሰነዶችን እንደሚፈራረሙም አክለው ገልጸወል፡፡
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ግንኝነትና ብሄረዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ በኢኮኖሚያዊ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በቀጠናው የጸጥታ ጉዳዮች ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ለመስራት ያላትን ቁርጠኛ አቋም አድንቀው የደቡብ አፍሪካ ኢንቨስተሮች የኢትዩጵያ መንግስት ባመቻቻቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ለአንባሳደሩ አብራርተዋል ፡፡
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ በመጠናቀቁ በአሁኑ ስዓት የፌዴራሉ መንግስት በጁንታው ኃይል ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ-ልማቶች መልሶ በመገንባትና የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ እንዲሁም ከአካባቢው ማሕበረሰብ የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም የሰብአዊ እርዳታ ድጋፎችን ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በሁሉም አቅጣጫ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በተቃራኒ በአንዳንድ ሚዲያዎችና የጁንታው ናፋቂ በሆኑ አካላት የሚሰራጨው ዜና እና ፕሮፖጋንዳ ሃሰት መሆኑን አብራርተወል፡፡
አክለውም በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚታየው የድንበር ውዝግብ በውይይት እና በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁመው ወደፊትም ኢትዮጵያ ለሁሉም የሰላም አማራጮች በሯ ክፍት ነው ሲሉ መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሁለቱ አገሮች ከግጭቱ የሚያተርፉት ምንም ነገር አለመኖሩንና ከዚህ ይልቅ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ፈትተው ወደቀደመው ታሪካዊ አጋርነታቸው ቢመለሱ በጋራ መልማት የሚያስችላቸው ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

