አዲስ አበባ ፣ የካቲት 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በደቡብ አፍሪካ ከአልጄሪያ አምባሳደር ረሺድ ነንሎነስ ጋር በሁለትዮሽና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የህግ ማስከበር እንቅስቃሴው በአብዛኛው እንደተከናወነ፣ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ ብቻ እንደሚቀር፣ በግጭቱ የወደሙ የክልሉን መሠረተ-ልማቶች በመጠገን ወደ ስራ የማስገባትና የሰብዓዊ ዕርዳታን ለማድረስ በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ዓለም-አቀፉ ሚዲያ ሁኔታውን በተገቢው መንገድ መዘገብ ላይ ያለበትን ክፍተት ኮንነዋል፡፡
የአልጄሪያው አምባሳደር በበኩላቸው÷ ሁኔታውን በሚገባ እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በአህጉሩ ካላት ከፍተኛ ቦታ አንጻር ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የድርድር ሂደት ያገጠሙ እንቅፋቶችን አስመልክቶ ሁለቱ አምባሳደሮች ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው የግድቡ ግንባታም ሆነ ድርድሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሌሎችን ባለመጉዳት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ስግብግብና ኢ-ምክንያታዊ አቋም ተገቢነት የጎደለው እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ረሺድ ነንሎነስ ኢትዮጵያ በድርድሩ ሂደት የያዘችውን አቋም አድንቀው በራሷ የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብቷን የሚከለክል ስምምነት ውስጥ አልገባም ማለቷ ተገቢና ትክክል ነው ብለዋል፡፡
በሱዳን መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ወረራን አስመልክቶ አምባሳደሮቹ በነበራቸው ውይይት መሰል ችግሮችን በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
አምባሳደሮቹ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ተቀማጭ በሆኑበት ደቡብ አፍሪካ ተደጋግፎ ለመስራት እንዲቻል ግንኙነታቸውን ቀጣይ ለማድረግ መስማማታቸውን በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መተግበሪያን https://play.google.com/store/apps/details?id=com.companyname.Fana
በስልክዎ በመጫን ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ኤፍኤም 98.1 እና ብሄራዊ ሬዲዮን ይከታተሉ፡፡ ቪዲዮዎችንም ይመልከቱ፡፡

