Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ24 ሰዓት ውስጥ አራት ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ አባዝተን እንሠጣለን በማለት ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ካሜሮናውያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር በ24 ሰዓት ውስጥ አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ አባዝተን እንሠጣለን በማለት ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ካሜሮናውያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በማታለል ወንጀል ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ካሜሮናውያን የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የገንዘብ ኖቶችን በ24 ሰዓት ውስጥ እያባዛን እንሰጣለን በማለት ሲያጭበረብሩ ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር በጋራ በተደረገ ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

በፓስፖርት ስማቸው ናዋ ሳምፕሰን እና ጁዲ አያምባንግ ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ካሜሮናዊያን ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው ማርክ እና ሳምሶን በሚሉ ሃሰተኛ ስሞች እንደሚጠቀሙ የጠቀሰው ኮሚሽኑ የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ጭምር እንዳላቸው በመናገር እና ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሲሆን የማታለል ተግባራቸውን ለመፈፀም ሲጥሩ በተደረገው የተቀናጀ ክትትል እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋን በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ቀጥረው በማግኘት “2 ሚሊዮን ትክክለኛ የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ይዘህ ከመጣህ በ24 ሰዓት ውስጥ በሁለት እጥፍ በማተም በአጠቃላይ አራት ሚሊዮን ዶላር ስለሚሆን 40 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ላንተ ቀሪውን 60 በመቶ ገንዘብ ደግሞ ለራሳችን እንወስዳለን” ብለው እንዲስማማ በማግባባት የማታለል ወንጀል ሲፈጽሙ እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በስምምነቱ መሠረትም ካሜሮናውያኑ አብሯቸው ለመሥራት የተስማማው ኢትዮጵያዊ ከተባዛው የአሜሪካን ዶላር ገንዘብ ውስጥ የሚገኝ የናሙና ገንዘብ ኖት ነው በማለት ነገር ግን ትክክለኛውን አንድ መቶ ዶላር በመሥጠት ወደ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሄዶ ወደ ኢትዮጵያ ብር እንዲቀይረው በማደረግ ጭምር የሚያባዙት የገንዘብ ኖት ትክክለኛና ህጋዊ ተቀባይነት ያለው እንደሆነ በማስመስል ግለሰቡን ለማጭበርበር እንደቻሉ ከተገኘው ማስረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ጉዳዩን አስመልከቶ መረጃ የደረሳቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትም ሁለቱ ካሜሮናውያንና በውጭ አገር ሆኖ ስምሪት የሚሰጣቸውን ግለሰብ ጨምሮ የሚያደረጉትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጥብቅ ሚስጥር በመከታተል ሃሰተኛ ገንዘብ ለማተም የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ መሣሪያዎች፣ የአሜሪካን ዶላር፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ገንዘብ፣ ድርሃምና የኬንያ ሽልንግ ትክክለኛ ገንዘቦችን ጨምሮ ሰነዶችና ፓስፖርቶች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርገዋል ።

ተጠርጣሪዎቹ የሃሰት ገንዘቦችን የማሠራጨት ሥራቸው እንዳይጋለጥ ግለሰቦችን ከእይታ ድብቅ በሆነ ሥፍራ ለማግኘት ከመሞከራቸውም በላይ በፓስፖርታቸው ላይ የሚገኘውን ህጋዊ ስማችውን በመቀየር እንዲሁም የካሜሮን ዜጋ ሆነው ሳሉ የደቡብ አፍሪካ ዜጋ እንደሆኑ ለተለያዩ ኢትዮጵያውን እራሳቸውን በማስተዋወቅ የማታለል ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታችውን የሚያስረዱ ማስረጃዎች መገኘታቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባደረገው ምርመራ የተገኙ ማስረጃዎች አመልክተዋል።

ተጠረጣሪዎቹ በተለይ 40 ሚሊዮን ዶላር ሃሰተኛ የአሜሪካ ዶላርን ለማባዛት የሚያስችላችው በዶላር መጠን የተቆራረጡ እና የታተሙ ወረቀቶች፣ ፓውደሮች፣ ማቅለሚያዎች፣ የዶላር መለያ ማሽኖች፣ ማድረቂያ መሳሪያዎችና ሌሎች ግብአቶችን ተጠቅመው እንዴት ሃሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን እንደሚያዘጋጁ ጭምር በመኖሪያ ቤታቸው ፖሊስ ብርበራ ባደረገበት ወቅት ማሳየታቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሷል ።

በተያያዘም ሀሰተኛ የኢትዮጵያን የገንዘብ ኖት በመስራት ወደ ገበያ እንዲገባ ሲያደርጉ ከነበሩ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ተጠርጣሪዎች መካከል ዮሴፍ ተከስተብርሃን እና ተክለብርሃን ገ/መስቀል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በቡድን በመደራጀት ሃሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን አትመው ሲያሰራጩ መቆየታቸውን የጠቆመው ፖሊስ ኮሚሽኑ ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት በተደረገባቸው ጥብቅ ክትትልና ድንገተኛ ፍተሻ 40 ሺህ ሃሰተኛ ባለ አንድ መቶ ብር የገንዘብ ኖቶች ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በቁጥጥር ስር ያልዋለውና የቡድኑ አባል የሆነው ሶስተኛው ተጠርጣሪ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ እንደነበረው በፖሊስ ምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ግለሰቡ ለጊዜው ቢሰወርም በደህንነትና በፀጥታ አካላት ክትትል ስር መሆኑን ፖሊስ ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡

በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን የሃሰተኛ ገንዘብ ህትመትና ዝውውርን ለመከላከል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ እና ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ የውጪ ሃገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውሶ በተለይም እንዲህ አይነቱ ወንጀል እንዲፈፀም የሚያመቻቹ እና ህብረተሰቡን የሚያሳስቱ ደላሎች መኖራቸውን በመገንዘብ የከተማችን ነዋሪዎች ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበሩ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መተግበሪያን https://play.google.com/store/apps/details?id=com.companyname.FanaAm በስልክዎ በመጫን ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት፣ ኤፍኤም 98.1 እና ብሄራዊ ሬዲዮን ይከታተሉ፡፡ ቪዲዮዎችንም ይመልከቱ፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version