Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዋጋ አተማመን አገልግሎት በቅርቡ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን በገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ የሚሰጠውን የዋጋ አተማመን እና የካርጎ ትራኪንግ አገልግሎት ስርዓትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገነፁት በገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ ሲሰራ የነበረው ወጥነት የሌለው አሰራር ክፍተት የተሞላበት ነበር፡፡

በሰው ኃይል ብቻ የሚከናወኑ ተመኖች ደግሞ የግልጸኝነት ችግር እንደነበረባቸው ነው ያስታወሱት፡፡

አሁን በቅርቡ ወደ አገልገሎት የሚገባው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዋጋ አተማመን አገልግሎት ዘርፉን ከማዘመኑም በላይ የጊዜ ብክነትንም የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል።

የካርጎ ትራኪንግ አገልግሎት ስርዓት አሰራሩ ከዚህ በፊት ዕቃ በመጉደልና በመጥፋት ደረጃ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ይፈታል ብለዋል።

በሌላ በኩል ተገልጋዮች በየቅርንጫፉ በመሄድ ይከፍሉ የነበረውን የቀረጥና ታክስ ክፍያን ባሉበት ሆነው በማንኛውም ባንክ በመጠቀም ወደ ኮሚሽኑ ሂሳብ የሚያስገቡበትን ስርዓት ከባንኮች ጋር ሰምምነት ተደርሶ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን ኮሚሽነሩ አክለዋል።

በሀገሪቱ በተቋም ደረጃ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያ ከተደረገባቸው ተቋማት አንዱ የሆነው ኮሚሽኑ የወረቀት አልባ አገልግሎቱን በመስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/
ዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም https://t.me/fanatelevision
ትዊተር https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version