Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኬንያ ከሚገኙ የሶማሌ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያን የሶማሌ ክልል ተወላጆች ጋር ውይይት መካሄዱን በኬንያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታወቀ፡፡

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ኬንያ ከሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ጋር በናይሮቢ በወቅታዊ ሃገራዊና የክልሉ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና የተለያዩ መስኮች ማሻሻያ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ያለው ለውጥ በሶማሌ ክልል ላይ ያስገኘውን ፋይዳ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በኬንያ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተወላጆችና ወዳጆች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንትና ንግድ እንዲሠማሩ፣ በቴክኖሎጂና ሣይንስ ሽግግር አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኬንያ የኢፌዴሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው የሶማሌ ኮሚዩኒቲ እስካሁን በኤምባሲው ባደረገው ድጋፍ አመስግነው ሚሲዮኑ ለዜጎች ሁልጊዜም ክፍት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በናይሮቢ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተወላጆች የሃገሪቱን ገፅታና የመንግስትን አቋም እንደሀገር አምባሳደርነታቸው በማህበራዊ ሚዲያ መስኮች እንዲያስተዋውቁም ጠይቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version