አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓድዋ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት አርማ በሚል መሪቃል በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ባደረጉት ንግግር ዘመነኛውን የጣሊያን ጦር ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ድባቅ የመቱበት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት ብርሃን የፈነጠቀ አኩሪ ድል ነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአድዋዎቹ ጀግኖች ያስረከቡንን ሃገር የዛሬው ትውልድ ጥንተ ጠላታችን ድህነትን በተባበረ ክንዳችን ድል መንሳት ይኖርብናል ሲሉም ንግግር አድርገዋል።
የአድዋ ድልን የተጎናፀፉ አርበኞች አርአያነት በመከተል ብዝሃነትን ለሃገር አንድነትና እድገት ማዋል ይኖርብናል ያሉት አቶ ከድር በተለይም ወጣቶች ከአድዋ ድል የተገኙትን አገራዊ ፍቅርን፣ አንድነትና የጀብደኝነት ትሩፋትን በተግባር በማሳየት የራሳቸውን ታሪክ መፃፍ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
አቶ መራድ በደዊ የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የዓድዋ ድል የጣሊያን ተስፋፊ በጀግኖች አባቶቻችን ድል የተመታበትና ኢትዮጵያ ነፃነቷን ያረጋገጠችበት ታላቅ ድል ነውና የጦርነቱን መንስኤ፣ የዲፕሎማሲ ጥረትና የጦርነቱን ድል ለወጣቱ ትውልድ በሚያሳይ መልኩ 125ኛው ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች በድሬዳዋ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከብሯል ብለዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር አቶ ይስሐቅ አለማየሁ በጦርነቱ መንስኤና የጦርነቱ ሂደትና ድሉን በተመለከተ ባቀረቡት ፅሑፍ የአውሮፓ ሃገራት አፍሪካን ለመቀራመት ባደረጉት ስምምነት ምስራቅ አፍሪካን ጣሊያን እንድትይዝ ቢስማሙም ጣሊያን አድዋ ድልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጊዜ ድል መደረጓን አስታውሰዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር በተከበረው 125ኛው የድል በዓል አከባበር ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብኅብ ክፍሎች ታድመውበታል።
በተሾመ ኃይሉ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

