Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም የአምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም የአምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

ድጋፉን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ረሺድ ከማል ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፣ ለትግራይ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሀም በላይ እና ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች አስረክበዋል።

አቶ ረሺድ፤ ኮርፖሬሽኑ ከባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ተቋማዊ ሕልውናውን በማጠናከር በተለያዩ መስኮች ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ባደረገው ጥሪ መሰረትም ለትግራይ ህዝብ ያለውን አጋርነት ለማሳየት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው ድጋፉ በአሁኑ ወቅት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ትልቅ አቅም መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህም ባሻገር የትግራይ ህዝብ በችግር ጊዜ አለኝታ እንዳለው የሚያረጋግጥበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በፌዴራልና በክልል መንግስታት ተቋማት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ለህዝብ አብሮነትና አንድነት መጎልበት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።

የትግራይ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሀም በላይ በበኩላቸው በትግራይ መልሶ ማቋቋም ስራ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ ሁሉም ዜጎች ለትግራይ ህዝብ አለኝታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

Exit mobile version