Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበት የዓድዋ ድል የአሸናፊነት ዋና መገለጫ በመሆኑ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበት የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ዋና መገለጫ በመሆኑ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
አቶ አደም ኢትዮጵያውያን ከዛሬ 125 አመት በፊት የመጣባቸውን የውጭ ወራሪ ኃይል ለመመከት በአንድነትና በሀገር ወዳድነት ወኔ ተነሳስተው የጋራ ውጤታቸው የሆነውን የአድዋ ድል በማስመዝገብ ለአፍሪካውያንና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ስነልቦና ምልክት የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ድል አበርክተዋል ብለዋል።
የካቲት 23 በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካውያንና በዓለም ጥቁር ሕዝቦች፣ የአሸናፊነት ስሜትና የነጻነት ጎሕ የተቀደደበት ቀን በመሆኑ የዓድዋ ድል ለትውልድ በማስተማር በስነልቦና የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው እንዲደገም መስራት እንደሚገባ በመጥቀስም የዓድዋ ድል አኩሪ ገድል በመሆኑ የዛሬ ትውልድ በኩራትና በነጻነት በዓለም አደባባዮች ላይ ቀና ብሎ እንዲራመድ ያደረገ ስለሆነ ሁልጊዜም ሊወደስና ሊዘከር ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ እንዲገን ካስቻሏት ውስጥ የዓድዋ ድል አንዱ ሲሆን የዓድዋ ድል ክብረ በዓል ለኢትዮጵያውያን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የነፃነት ብቻ ሳይሆን የአንድነት ዓርማ ፣ የብዝኃነትና የጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ የምርምርና ጥናት ምንጭ እንዲሆን መሰራት አለበት ብለዋል አፈ ጉባዔው ።
ከዓድዋ ድል በመማርም ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷን በማጠናከር አዲስ የታሪክ አሻራ ለማኖር በትብብር መስራቱ ኢትዮጵያ የታላቅ ህዝብ ሀገር መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች የምትሄድ አፍሪካዊት ሀገር ያደርጋታልም ነው ያሉት።
በመጨረሻም የአንድነትና የጋራ ውጤት የሆነው የዓድዋ ድል በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የምትታወቅ ኢትዮጵያ፣ ለተግዳሮት እጅ እንደማትሰጥ ማሣያ በመሆኑ የሁሉም ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል ለዚህ ህያው ምስክር ስለሆነ የይቻላል መንፈስን ከዓድዋ ድል በመማር በየወቅቱ ሀገሪቱን የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በድል አድራጊነት ወኔ መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version