Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኩባ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር የኩባ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኩባ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አናያንሲ ሮድሪጌዝ ካሜጆ ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በቀጠናዊ፣ በሁለትዮሽና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ሽብሩ ማሞ መንግስት ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በትግራይ ክልል እያደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ አሰጣጥ በተመለከተ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት አስረድተዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ውይይቱ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ እንዲጠናቀቅ እያደረገች ያለውን ያላሰለሰ ጥረት እና ውይይቱ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለምክትል ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
ምክትል ሚኒስትሯ በበኩላቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስታውቀው ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር አሁንም በአለም አቀፍ መድረኮች እና በሌሎች በተለያዩ ዘርፎች ተባብራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።
በመጨረሻም በቀጠናዊና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለተደረገው ገለጻ አመስግነው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በቅርበት እንደሚከታተሉና አስፈላጊ በሆነበት ወቅትም ከሚሲዮናችን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version