አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የምርጥ ዘር ብዜት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በመገምገም ዘርፉን ማዘመን የሚያስችል ከፌዴራል፣ ክልሎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደገለጹት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በቴክኖሎጅ መደገፍ እና በተለይም ደግሞ የግብዓት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ስራ በመስራት የምርጥ ዘር አቅርቦትን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የስርዓተ-ምግብን እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላለው 38 በመቶ የህጻናት መቀንጨር ምክንያት የሆነውን የምግብ እጥረት ለማስቀረት ብሎም ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎች እና ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የአገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ማምጣት እንደሚቻል ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልፀዋል፡፡
የግብርና ግብዓት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ በበኩላቸው በዘር እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን አጠቃላይ የአሰራር ሂደት እና በየክልሎች የተሰራጨውን እና የተሰበሰበውን የዘር ብዜት በመግለፅ በቀጣይ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ግብዓት ዋናውን ድርሻ እንደሚወስድ እና በአሁኑ ወቅትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን አጠቃላይ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ባለው የዘር ብዜት እና ስርጭት ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እና የተጠናከረ የግብርና ምርምር ተቋማት እንዲሁም ዘርፉን የሚያበረታታ ፖሊሲ ተቀርፆ ድጋፍ ካልተደረገ የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ማሳደግ አይቻልም ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

