አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራት የዝናብና ውሃ እጥረታቸውን ለመፍታት ከከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ እስከ ደመና ማዝነብ የደረሱ የተለያዩ አማራጮችን እንደሚጠቀሙ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ደመና ማዝነብ እየተለመደ የመጣ የሳይንስ ግኝት ነው ያለው ሚኒስቴሩ ደመና ከመሬት ከፍ ብሎ በሚገኝ ከባቢ ላይ በትነት መልክ የሚገኝ የውሃ ስብስብ ቅንጣት መሆኑን ገልጿል።
ይህ በሚሊየን የሚቆጠር ወደዝናብ ያልተቀየረ ነጠብጣብ /ቅንጣት/ በንጥረ ነገር ርጭት አማካኝነት ከነጠብጣቡ ከፍ ብሎ እንዲያድግና ወደ መሬት ዝናብ ሆኖ እንዲወርድ ማድረግ የሚቻል ሲሆን ይህ ዳመና ማዝነብ (cloud seeding) ይባላል ነው ያለው።
ደመና ያለበት አካባቢ ላይ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት የሚደረግ ሲሆን ንጥረ ነገሩ (ሲልቨር አይወዳይድና ፖታሺየም አይወዳይድ) ተበታትኖ የነበረው ደመና ላይ ሲያርፍ ደመናው እንዲሰበሰብና ወፈር ወዳለ የውሃ እንክብል እንዲቀየር ያደርገዋል።
ይህ የውሃ እንክብል በመሬት ስበት አማካኝነት ወደ መሬት እንዲዘንብ ይገደዳል።
የንጥረ ነገር ርጭቱ ሀገራት እንዳላቸው አቅም ከመሬት ወደ ደመናው መርጭትም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች አሉ ተብሏል።
በሮኬት መልክ መተኮስ የሚቻል ሲሆን በሰው አልባ አውሮፕላኖችም ርጭት ማድረግ የሚቻል ሲሆን የተለመደው ግን በአውሮፕላን ከደመናው በላይ አልያም በታች እየበረሩ መርጨት ነው።
ኢትዮጵያ ሰሞኑን የሞከረችው በአውሮፕላን የሚረጨውን ሲሆን ከደመናው ስር በመሆን ንጥረ ነገሩን በአውሮፕላን የሚረጭበት ነው።
የተለያዩ የዳመና አይነቶች ሲኖሩ ይህኛው ዳመና የሚስብ/የሚነፍስ ንፋስ ስላለው ንጥረ ነገሩ ከስሩ ሲረጭ ከደመናው ጋር ወስዶ ይቀላቅለዋል።
ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከመሬት ላይ በሚተከል “ግራውንድ ጀኔሬተር” አማካኝነት ዝናብ ማዝነብ ሲሆን እዚህ ላይም ኢትዮጵያ ስራዎችን እየሰራች ነው ተብሏል።
ንጥረ ነገሩን የሚረጭ “ግራውንድ ጄነሬተር” እንጦጦ ላይ ተከላ እያካሄደች ነው። ይህኛው አሰራር ተራራማ ቦታዎች ላይ ተተክሎ ከመሬት ቅርብ ወደ ሆነ ዳመና ንጥረ ነገር እንዲረጭ የሚደረግበት ነው። ቁጥጥሩ ደግሞ ከሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ባለ ማዕከል ላይ ይደረጋል።
ይህንን ስራ ለመስራት ኢትዮጵያ የተጠቀመችው ንጥረ ነገር በዋጋው ዝቅተኛ የሆነውን ሶዲየም ክሎራይድና ፖታሺየም ክሎራይድ ድብልቅ (ሃይድሮስኮፒክስ) የተሰኘውን ንጥረ ነገር ነው።
ይሄ ቴክኖሎጂ በተፈጥሮ የሚገኝ ደመናም ይፈልጋል የተባለ ሲሆን አየር ላይ ደመና ከሌለ ዝናብ ማመንጨት እንደማይችልና ቴክኖሎጂው ደመና መፍጠር የሚያስችል አቅም ላይ እንዳልደረሰ ተጠቁሟል።
ይህንን ከደመና ዝናብ የማመንጨት ቴክኖሎጂ እስራኤል፣ ቻይናና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በተለያየ መልኩ እንደሚጠቀሙበትና በረሃማ ቦታዎቻቸውን ማልማትም መቻላቸው ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ይህንን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ስታውል የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጓ እና የኢትዮጵያ ባለሙያዎችም በሰፊው መሳተፋቸው ታውቋል።
ከበረራ ጋር በተያያዘም የኢፌዴሪ አየር ሃይል የጥገና ባለሙያዎችና አብራሪዎች ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስጀመሩትና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራው ይህ ስራ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት፣ የብሄራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ፣ የተፋሰስ ባለስልጣን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎ ማዕከል፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲቲዩት፣ የኢንፎርሜን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት እና ከግሉ ዘርፍ ድሮን ላይ የሚሰሩ ቡድኖች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ዓለም ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ብቻ ሳይሆን መፍጠርንም መማር አለባት ያሉት የኢኖቬሽናን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ ኢትዮጵያም ይህን ቴክኖሎጂ በረሃማ ቦታዎችን ለማልማት በሰፊው ጥቅም ላይ ታውለዋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በረሃማና ከፍተኛ የውሃ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን ለማልማት የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ሂደት በቅርቡ እንደሚጀመር ይፋ አድርጋ ነበር።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን