አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ጥራት የሌላቸው ምርቶች ገበያ ላይ እየታዩ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስጠነቀቀ።
ባለስጣኑ በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጥራት የሌላቸውን ምርቶች ለገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች መኖራቸውን አስታውቋል።
በተለይ ይህ ችግር በዘይትና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ በስፋት የሚታይ መሆኑም ነው የገለጸው።
የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለ ስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ÷ የደረጃ ምልክት፣ የምርት ጊዜና አድራሻ የሌላቸው የዘይት ምርቶች ገበያ ላይ እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት በርበሬን የካንሰር ህመም ሊያስከትል ከሚችል ቀለም ጋር እንዲሁም ሌሎች ምግብ ነክ ግብአቶችን ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች ጋር ቀላቅለው ለገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች መኖራቸውን ዳይሬክተሯ ገልጿል።
ባለስልጣኑ እንዲህ አይነት ተግባር በሚፈፅሙ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በየደረጃው ካሉ የህግና የፍትህ አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ህብረተሰቡ የሚገዛቸው ምርቶች የጥራት ደረጃ፣ የምርት ግዜና አድራሻ እንዳለባቸው መለየት አለበት ብሏል።
በተጨማሪም ምርቶቹን ሲገዛ ደረሰኝ መጠየቅ እንዳለበትና የተለየ ነገር ሲገጥመው በ8482 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ለሁለት ቀናት የሚቆይ የምክክርና የህዝብ ንቅናቄ መድረክ በጅማ ከተማ እያካሄደ ነው።
በሙክታር ጠሃ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

