Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ባካሄደው የተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት አዲስ አበባን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን 359 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።
ኮሚሽኑ የፀጥታ ስራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣የተሽከርካሪ ስርቆት፣ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠርጣሪዎችን ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኙ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 7 የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ህብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች 8ቱ እንደተያዙና የሁለቱ መኪኖች አካላቸው እንደተፈታታ ገልጿል፡፡
ከዚህ ወንጀል ጋር የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችም ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ተመልክቷል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
እንዲሁም ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ ተችሏል፡፡
ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ምስጋና ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version