አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በእነ ጃዋር መሀመድ ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክር በግልጽ ችሎት እንዲሰማ የሰጠው ብይን ታገደ።
እግዱን የጣለው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው።
ባሳለፍነው ማክሰኞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጸረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ህግ በምስክር ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በመጥቀስ 146 ምስክሮቼ በየደረጃው በዝግ ችሎት ከመጋረጃ በስተጀርባ ምስክርነታቸው ይሰማልኝ ብሎ ያቀረበውን ማመልከቻ በቂ ምክንያት አደለም ሲል ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
እንዲሁም ተከሳሾቹ ምስክሮቹ በዝግ ችሎት ሊሰሙ አይገባም የመከላከል መብታችንን የሚያጣብብ በመሆኑ የዐቃቤ ህግ ጥያቄ ውድቅ ይደረግልን ሲሉ ያቀረቡትን መቃወሚያም ችሎቱ መርምሮ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ በግልጽ ችሎት ምስክር እንዲሰማ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
በዚህ ብይን ላይ ቅር የተሰኘው ዐቃቤ ህግም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ሲል አመልክቷል።
ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በእነ ጃዋር ላይ የሚሰሙ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ የሰጠውን ብይን እግድ በመጣል በጉዳዩ ላይ ለማከራከር ለሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ. ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

