አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ህገወጥ ተግባራትን የፈፀሙ ከ200 በላይ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ እንደገለጹት፤ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ቦርድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባደረገው ክትትል ሠራተኞቹ በርካታ የአሰራር ጉድለቶችን መፈፀማቸውን አረጋግጧል።
በዚህም ተገልጋይን በአግባቡ አለማስተናገድን ጨምሮ እስከ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት የተመዘገበባቸው ሠራተኞች እንደሚገኙ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ጉድለት በፈፀሙ ከ200 በላይ ሠራተኞች ላይ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ 14 ዓመት የሚደርስ የእስራት እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች ከፈፀሟቸው ስህተቶች ውስጥ ደንበኛን አለማክበር፣ ሱቅ ዘግቶ መጥፋት፣ ምርትን ባልተገባ መንገድ ለመሸጥ ሲያወጡ እጅ ከፍንጅ መያዝ እና የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሂሳብ ማጉደል ይገኙበታል።
በዚህ ዓመት ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ዓላማውም ሌሎች ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ ለማስተማር ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 148 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ይገኛሉ።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

