አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከክልል ስራ እድል ፈጠራ አካላት ጋር በመሆን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀሙንና የመረጃ ጥራት ዳሰሳ ጥናት ግምገማ በሀዋሳ አካሂዷል፡፡
ኮሚሽኑ ይፋ እንዳደረገው የተፈጠረው የሥራ እድል የአመቱን አቅድ 94 በመቶ ያሳካ ነው፡፡
በግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፍ ከተፈጠረው የሥራ እድል ውስጥ 64 በመቶ ቋሚ ሲሆን፥ ቀሪው ጊዜያዊ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኢፌድሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን፥ ካለፉት ዘጠኝ ወራት የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመጠቀምና ክፍተቶችንም በመለየት ለቀጣይ እቅድ የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ መድረኩ ያግዛል በልዋል፡፡
የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች በተጨማሪ በ10 ዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ ውስጥ ተለይተው ከተቀመጡት 11 ዘርፎች ከክልሎች ጸጋዎች ጋር የሚሄዱን መርጡ የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ የሚያግዙ ግብዓቶች ከጉባዔው እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ዘንድሮ በገጠርና በከተማ በተደረገው እንቅስቃሴ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል 35 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመድረኩ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲን ጨምሮ የክልል ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ተጨማሪ መረጃ:- ከኮሚሽን ማህበራዊ ትስስር ገጽ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

