አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከ700 ሺህ በላይ ኩንታል የምግብ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል መላኩን አስታወቀ።
ካለፈው ወር አንስቶ በትግራይ ክልል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ 86 በመቶ የቆዳ ስፋት በአጋር አካላት ቀሪው 14 በመቶ ደግሞ በመንግስት እንደሚሸፈን መገለፁ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ምዕራብ ዞን፣ ደቡብ ዞን አምስት ወረዳዎች፥ በመንግስት የሚሸፈኑ ሲሆኑ ደቡብ ሶስት ወረዳዎች፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ እና የመቐለ ከተማ ደግሞ በአጋር አካላት የሚሸፈኑ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚሽኑ በግጭትም ሆነ በሌሎች የአደጋ ክስተቶች ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ያደርጋል።
ኮሚሽኑ በአማራ፣ ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ጊዜያዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በትግራይ ለ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሶስተኛ ዙር ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ በመንግስትና በዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት እየተሰጠ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ቀደም ሲል ድጋፉ 70 በመቶ በመንግስት ቀሪው 30 በመቶ በአጋር አካላት ይቀርብ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ 86 በመቶ በአጋር አካላት 14 በመቶ ደግሞ በመንግስት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
እስካሁን ባለው ለትግራይ ክልል 772 ሺህ 954 ኩንታል እህልና 289 ሺህ 339 ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ መላኩንም ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ኀብረተሰቡ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችም መሰል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ 124 ሺህ 49 ኩንታል እህል እንዲሁም በአማራ ክልል አጣዬ የተፈናቃዮች 32 ሺህ 520 ኩንታል ምግብ ተልኳል ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!