Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በያቤሎ ከተማ ከ172 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአግልግሎት በቅተዋል

 

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቦረና ዞን በያቤሎ ከተማ ከ172ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የተመረቁት 16 ፕሮጀክቶች የመብራት ማከፋፈያ ጣቢያ፣የያቤሎ ከተማ ሆስፒታል ማስፋፊያ፣የተለያዩ የኮብልስቶን መንገዶች እና ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ እና የቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጉዮ ገልገሎን ጨምሮ የክልሉና የዞኑ አመራሮች እንዲሁም የአከባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ነው የተመረቁት።
በዛሬው እለት የከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የመብራት ስቴሽኑ ከከተማው አልፎ የዞኑን የተለያዩ ወረዳዎች በመድረስ የመብራት ፍላጎታቸውን ከማሟላት አልፎ አከባቢው ላይ ለሚካሄድ ኢንቨስትመንትም አጋዥ እንደሚሆን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጉዮ ገልገሎ ገልጸዋል።
የዛሬውን ጨምሮ በዚህ ሳምንት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ከ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 136 ፕሮጀክቶችም እንደሚመረቁ ነው አስተዳዳሪው አክለው የገለፁት።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪው አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፥ በዘንድሮው ዓመት በክልሉ የህዝቡን ችግር ሊቀርፉ የሚያስችሉ ከ31 ቢሊዩን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ከ11 ሺ በላይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ይውላሉ።
ክልሉም ለመሰል የፕሮጀክቶች የተለየ አመራርን የሚሰጠው፥ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት በማዋል ህዝቡን በኢኮኖሚ እራሱን ለማስቻል፣በቴክኖሎጂ እና በእውቀት ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር እና ቀጣይነት ያለው የተቋም ግንባታን መፍጠርን ዓላማ አድርጎ መሆኑን ነው የገለፁት።

 

በትዝታ ደሳለኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version