አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የነቀምት_ሶጌ_ካማሺ_ቆንጮ 160 ኪ ሜ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በ4ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግንባታው ተጀመረ።
በመንገድ ማስጀመሪያ መረሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ፣የቤኒሻንጉል ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ መንግስት የህዝቡን የመሠረተ ልማት ችግሮች ለመቅረፍ እየሠራ ካሉት ተግባራት መካከል ክልሎችን እና አጎራባች ሀገራት ጋር ሀገራችንን የሚያገናኙ መንገድ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል ብለዋል።
የመንገዱ መገንባት አካባቢዎች ያሏቸውን የኢኮኖሚ አማራጮችን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
የቤንሻንጉል ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ÷የሁለቱን ህዝቦች የኖረ ግኑኝነት ለማጠናከር መንገዱ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ በአብሮነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ÷ መንገዱ በ4ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን የግንባታ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መንገዱ በገጠር ከ8 እስከ 10ሜ እንዲሁም በወረዳ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ከ19 እስከ24 ሜ ስፋት ኖሮት እንደሚገነባ ጠቁመዋል።
የመንገዱ መገንባት በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ እና የሀገሪቱን የቱሪዝም ፍሰት ለማሳደግም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል ።
በተጨማሪም ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ በነቀምት ከተማ በ7ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለሚገነባ የነቀም የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታንም አስጀምረዋል።
በቅድስት ብርሃኑ እና አፈወርቅ አለሙ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

