አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመቐለ ከተማ በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ የሰለጠኑ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደ ስራ መግባታቸውን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በጽህፈት ቤቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አስተባባሪ አቶ ሃይላይ ገብረ ጊዮርጊስ ÷ከዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተመረቁ 1 ሺህ 80 ወጣቶች በጌጠኛ መንገድ ድንጋይ ንጣፍ ሙያ ለሦስት ወራት ሰልጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል ።
ወጣቶቹ አሁን ላይ በሰባት ክፍለ ከተሞች 15 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላቸው የጌጠኛ ንጣፍ መንገዶች ስራ መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
ወጣቶቹ ስራውን በጥራትና በፍጥነት እንዲያከናውኑ የብቃት መመዘኛ ፈተና ወስደው ያለፉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የከተማው መስተዳድር ለጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ 117 ሚሊየን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በሚቆጥቡት ገንዘብ ወደ ግላቸው ስራ እንዲሸጋገሩ የሚያግዛቸው የንግድና ሌሎች የሙያ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል።
በማህበር ተደራጅተው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል የሃውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አሰፋ አብርሃ ÷“በዘርፉ የተፈጠረው የስራ እድል ያለብንን ኢኮኖሚ ችግር ያቃልልናል” ብሏል።
ከዘርፉ የምታገኘውን ገንዘብ በመቆጠብ ወደ በሌላ የግሏ ስራ ለመሰማራት ማቀዷን የገለጸችው ደግሞ የዓዲሽ ምዱሑን ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አስቴር ሃብታሙ ነች።
በምህንድስና ሙያ ከሁለት ዓመት በፊት የተመረቀችው ወጣት ሰናይት መብራቱ በበኩሏ ከጌጠኛ ድንጋይ ማንጠፍ ስራው ልምድ እንድታገኝ እንደሚረዳት መግለጿን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

