Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በፍቅር፣ በመተሳሰብና በይቅርታ ስንሰባሰብ ጠላቶቻችን አይወዱም – ሌ/ጄነራል አስራት ዴኔሮ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረ-ብሔራዊነታችን የውበታችን መገለጫና የጥንካሬያችን ምንጭ ነው ፤ ሰላም ለሁሉም- ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ ቃል በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ከተማ የዕርቀ ሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ ÷ ከዞኑ ተፈናቅለው የነበሩ ከ 50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወደ ወረዳቸው መመለስ የቻሉት በህብረተሰቡ ተሳትፎና ታጣቂዎቹ የሰላም አማራጩን ተቀብለው በመግባታቸው እንዲሁም ሰላሙን ለማምጣት የፀጥታ ሃይሉ በከፈለው መስዋዕትነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ለሰላም በፍቅር ስንሰባሰብ ጠላቶቻችን አይወዱም ያሉትሌተናል ጄነራል አስራት÷ በመሆኑም የጠላቶቻችንን ሴራ በማወቅ ልንታገላቸውና ልናጋልጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋስ በበኩላቸው ÷ይቅርታው ከልብ ሊሆን ይገባል ያለፈውን በመተው ለቀጣይ የዞናችን ሰላምና ልማት መትጋትና መዘጋጀት እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

በተመሳሳይ የማንዱራ ወረዳ የፎቶ ማንጃሬ ቀበሌ ነዋሪዎችም የእርቀ ሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል።

በዕርቀ ሰላሙ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት÷ ዕርቀ ሰላም መፈጠሩ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ ÷ ይህ ሰላም እንዳይቀለበስ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል።

ጫካ ገብተው የነበሩና የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ማዕከል ገብተው ወደ ወረዳቸው የተመለሱ የመጀመሪያው ዙር የታጣቂዎቹ አመራሮችም ህዝቡን በድለናል ይቅርታም ይደረግልን ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የአማራና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቢሮ ኃላፊዎች ፣ የሰራዊቱ አዛዦችና የወረዳ አሰተዳደሮችን ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ይህ የሰላምና የዕርቅ ኮንፈረንስ በቡለን ፣ በማንዱራ ፣ በዳንጉርናበ ፎቶ ማንጃሬ ቀበሌዎች የተደረገ ሲሆን÷ በቀጣይም በሁሉም የዞኑ ቀበሌዎች ድረስ እንደሚካሄድ ከመከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version