አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልልየቱሪዝም የታክሲ ማህበር በቢሾፍቱ ከተማ ተመሰረተ።
በቱሪስት መስህብነት በምትታወቀው ቢሾፍቱ የተመሠረተው የታክሲ ማህበሩ ከስራ እድል ፈጠራ ጎን ለጎን የከተማዋን ብሎም የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል፡፡
‘አደኣ ታክሲ’ በሚል ስያሜ ዘመናዊ የሜትር ታክሲዎችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት በቢሾፍቱ ከተማ እና አካባቢው ለሚመጡ ቱሪስቶች ጥራቱን የጠበቀ የትራንስፖት አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተመሠረተ ሲሆን÷ ይሄ ማኅበር በክልሉ የመጀመሪያ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
በምስረታው ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ እንዳሉት ÷ መንግስት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት እቅድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ሴክተሮች መካከል ቱሪዝም ከቀዳሚዎቹ ውስጥ ነው ብለዋል፡፡
ሃላፊው አያይዘውም በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም መስህብ ሀብትን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለውጦ ለሀገር እድገት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም መስህቦች በቅርበት በሚገኝባት ቢሾፍቱ ውስጥ የቱሪዝም ታክሲ ማህበር መቋቋሙ ደግሞ ለዘርፉ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የማህበሩ አባላት በጥሩ ስነ ምግባር ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የከተማማዋን እና የክልሉን መልካም ገጽታ በመገንባት ላይ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
60 ዘመናዊ ታክሲን በአባልነት ይዞ የተቋቋመው ማህበራቸው ለ210 ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥር እና ጥራት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል፡፡
የማህበሩ አባላት በበኩላቸው÷ ባለሀብቶች እና ወጣቶች በዚህ መልኩ ተቀናጅተው ዘርፉን ቢያገለግሉ የቱሪስቶችን ደህንነት በመጠበቅ የሀገሪቱንና የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

