አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) ዘርፉ የሚመራበትና ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጅ መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስትም የዘርፉን ችግሮች በመለየት ያለውን እምቅ ሀብት ለመጠቀም ያስችል ዘንድም በራሱ የሚመራበት መዋቅር ዘርግቷል ብለዋል።
የተዘረጉት አሰራሮች አርሶ አደሩን ከባለሀብቱ ጋር የሚያቀናጁ እንዲሁም÷ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰፊ ግብአት ማቅረብ እንዲቻል የሚያደርጉና የውጭ ምንዛሬ እና የስራ እድል ፈጠራውን የሚያሳድጉ ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ የሆልቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዱ በበኩላቸው እየተሰሩ ያሉ ጅምር ስራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ ነው ይላሉ።
ነገር ግን አሁንም የመሰረተ ልማት፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችና መሻሻል ያለባቸው መሰል ችግሮችን መፍታት ከተቻለ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት ብሎም የስራ እድል ፈጠራውን ማሳደግ ላይ የሚኖረው ድርሻ ቀዳሚ ይሆናል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
አሁን ያሉትን መልካም እድሎች በማየት የውጭ ባለሀብቶች ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ15 በላይ የውጭ ባለሀብቶች ጥያቄ ማቅረባቸውን እና 2 ሺህ ያህል ሄክታር መሬትም ለዘርፉ ኢንቨስትመንት መጠየቁን ተናግረዋል።
አሁን ጥያቄ ያቀረቡት ባለሀብቶች ወደ ስራ ሲገቡ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል።
ከአበባ እና አትክልት ዘርፍ ባለፉት 11 ወራት 485 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ቀሪውን አንድ ወር ጨምሮ በአመቱ 525 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በዙፋን ካሳሁን
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

