አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋና ላምሮት የምዕራፍ 7 የፍፃሜ ውድድር በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡
ለፋና ላምሮት የምዕራፍ 7 የፍፃሜ ውድድር አሸናፊዎችም 500,000 ብር ተበርክቷል፡፡
በምዕራፉ ተሳታፊ ለመሆን ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ወጣት ድምፃውያን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ተመዝግበው የማጣሪያ ውድድር አድርገው ነበር፡፡
ማጣሪያውን ያለፉ 12 ድምፃውያን በየሳምንቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ከሙሉ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመሆን በዳኞችና በራሳቸው የተመረጡ ዘፈኖችን እያቀረቡ ተወዳድረዋል፡፡
በተመልካች የSMS ድምጽ እና በሙዚቃ ባለሙያ ዳኞች ድምር ውጤት ዝቅተኛ ያገኝ አንድ ተወዳዳሪ በየሳምንቱ እየተሰናበተ አራት ድምፃውያን ቀርተው ዛሬ የፍጻሜ ውድድር በ3 ዙር አካሂደዋል፡፡
በቀጥታ ስርጭት በተካሄደው በዛሬው የፍጻሜ ውድድር ድምፃዊ ተስፋ ልደት ታደሰ አንደኛ በመውጣት የምዕራፉ አሸናፊ በመሆን 200,000 ብር ተሸልሟል፡፡
ድምፃዊ ሔኖክ ጥጋቡ ደግሞ ሁለተኛ በመውጣት 150,000 ብር ተሸልሟል፡፡
ድምፃዊ ቢንያም አስናቀ ሦስተኛ፣ድምፃዊ ማኅደር ደመላሽ አራተኛ በመውጣት 100,000 ብር እና 50,000 ብር አግኝተዋል፡፡
አንጋፋው ድምጻዊ ፀጋዬ እሸቱ በክብር እንግድነት ተገኝቶ ለአሸናፊዎቹ ሽልማቱን አበርክቷል፡፡የሞያ ህይወቱንና ውጣውረዱን ለድምጻውያኑ አካፍሏል።ዝናን በሚገባ የመያዝና ሞያን የማሳደግ ጥበብን በተመለከተ ምክር ሰጥቷል።
በእለቱ ተገኝተው ለተሳታፊ ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት የሰጡት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የይዘት ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰጠኝ እንግዳው÷ ባስተላለፉት መልዕክት ፋና በሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እና ሞያና ሞያተኛን በቀጥታ በማሳተፍ ጥበብን ሁለንተናዊ ግልጋሎት እንዲሰጥ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዛሬን ጨምሮ በያዝነው ዓመት በተካሄዱት 3 የምዕራፍ ውድድሮች ለፍጻሜ የደረሱ ተወዳዳሪዎች የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ያካሂዳሉ።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለሚጀምረው እጅግ አጓጊውና ከፍተኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር 1 ሚሊየን ብር እና ልዩ የክብር ዋንጫ ለሽልማት ተዘጋጅቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

