አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ወጣቶች በሰላም ዙሪያ ግንዛቤ የሚለዋወጡበትና ችግኝ የሚተክሉበት የሁለት ቀናት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
“ወጣቶች ሰላምን ያንጻሉ፤ አካባቢን ይንከባከባሉ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ሁነት የምስራቅ አፍሪከ ተጠባባቂ ሃይል ከኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።
ነገና ከነገ በስቲያ በሚካሄደው በዚሁ ሁነት ከምስራቅ አፍሪከ ተጠባባቂ ሀይል አባል አገራት ከተወጣጡ ወጣቶች በተጨማሪ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችም ይሳተፋሉ ተብሏል።
ጉዳዩን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጽጌሬዳ ዘውዱ÷ ሁነቱ “የኢትዮጵያን እናልብስ” አላማን ለማስፋት ይረዳል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን እስካሁን በአገር ደረጃ ሲሰራ የቆየውን የችግኝ መትከል ስራም ወደ ቀጠናው ለማስፋት እንደሚረዳም ነው የገለጹት።
በዚሁ ተግባር 80 ወጣቶች እንደሚሳተፉ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቷ ÷ 70 ገደማ የሚሆኑት ከአገር ውስጥ ሲሆን የተቀሩት ከተጠባባቂ ሀይሉ አባል አገራት እንደሚሆኑም ተናግረዋል።
የአፍሪከ ሕብረትና የተለያዩ የሲቪክ ማሕበራት ተወካዮችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል የሰላም ማስፈን ክፍል መምሪያ ብርጋዴር ጀነራል ሄንሪ ሱኬም በበኩላቸው÷ የቀጠናው ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ወጣቶቹ ችግኝ ሲተክሉና አካባቢያቸውን ሲንከባከቡ ለቀጠናው ሰላምና ደህንነትም በጎ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ነው ያሉት።
ይህ ተግባር ምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገራት ትብብራቸውም እንዲጠናከር እድል የሚፈጥር መሆኑን ነው የገለጹት።
ብርጋዴር ጀነራል ሄንሪ በእስካሁኑ ሂደት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የወሰደችሁ ተነሳሽነት የሚደገፍና የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
“እስካሁንም በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ መትከሏን ግንዛቤ አለን÷ሁኔታው የአካባቢው አገራትንም የሚያነሳሳ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አስር የምስራቅ አፍሪከ አገራትን በአባልነት የያዘ ቀጠናዊ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!