አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከልን የኦክስጅን ምርት ለማሳደግ የሚረዳ የአንድ መቶ ሲሊንድር እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ቁሳቁሶች ግዢ ተፈጽሞ ርክክብ ተደርጓል፡፡
በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲቲዩት የአስተዳደርና ልማት ቺፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዝናሽ ሠለሞን÷ በማዕከሉ የተጀመረዉን የኦክስጅን ምርት፣ በሙሉ አቅም ሥራ ለማስጀመር እና አቅርቦቱን ለማሳደግ ከሚረዱት ዉስጥ የሲሊንደር አቅርቦት አንዱ ነዉ ብለዋል፡፡
በጅማ አደጋ ጊዜ ክወና ማዕከል በኩል የተገዛው ሲሊንደር ከ1ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
የሲሊንደሩ አቅርቦት የኦክስጅን ፈላጊ ታካሚዎችን ፈተና የሚቀርፍ በመሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የጅማ አደጋ ጊዜ ክወና ማዕከል ኮሚቴን ወክለዉ የተገኙት አቶ ተመስገን ቃበታ÷ በአሁኑ ወቅት የጅማ ህክምና ማዕከል በየቀኑ ከሚያስተናግደዉ የኦክስጅን ታካሚዎች ቁጥር አንጻር ተመጣጣኝ አለመሆኑን በመገንዘብ አቅርቦቱን ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የሲሊንደር እና አስፈላጊ የሆኑ የቁሳቁስ ግዢ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ክሊኒካል ቺፍ ዳይሬክተር ዶክተር ፈቲያ አወል በበኩላቸዉ÷ በርካታ ሰዎች የኦክስጅን አገልግሎት ለማግኘት እንደሚፈልጉ ገልጸው፣ ይህ ተግባር የኦክስጅን ህክምና አቅርቦትን ለማሳደግ የሚረዳ ነዉ ብለዋል፡፡
የጅማ አደጋ ጊዜ ክወና ማዕከል የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ጥራት ያለዉ የኦክስጅን ማምረቻ ሲሊንደር ገዝቶ በማስረከቡ ምስጋና ይገባዋልም ብለዋል፡፡
በተመስገን አለባቸው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

