አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ኮቪድ 19 ካሳደረው ተፅዕኖ ለመላቀቅ ከተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
“የዲጂታል ትብብር የኮቪድ 19 ተፅዕኖን ለመቋቋምና በዘላቂነት ለማገገም” በሚል መሪ ቃል አለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ህብረት ያዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተቋቁሞ ለማገገምና ለመጠናከር ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስለሚጫወተው ሚና ለህበረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የዓለም ኢኮኖሚ ለመጠገን የዲጂታል ትብብር እና ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ትብብር መስክ ከአለም ባንክ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከኢስቶኒያና ከሌሎች ሀገራትና ድርጅቶች ጋርም በትብብር እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየሰራቻቸው ያሉ የማሻሻያ ስራዎች በበይነ-መረብ ግንኙነት ችግር ተፈትነዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ ይህንን ለመቅረፍ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።
የዩኒሴፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ፋያዝ ኪንግ በበኩላቸው÷ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የሚሆኑ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ቤቶችን ከበይነ መረብ ጋር በማገናኘት በዲጂታል ትምህርት መስጠት ላይ ሲሰራ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡
በመድረኩ የተባበሩት መንግስታትና የልዩ ልዩ ሀገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን÷ የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ያሳደረው ተፅዕኖና ከተፅዕኖው ለመውጣት የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

