Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በተያዘው የበጀት ዓመት ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሀረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው 2013 የበጀት አመት በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ የሀረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩሱፍ እንደገለፁት÷ በክልሉ በተያያዘ የበጀት አመት 11 ወራት ውስጥ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።
ይህም በዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 88 በመቶ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ገቢው የተሰበሰበውም ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆነ የታክስ እና ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ገቢዎች መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከቀጥታ ታክስ 374 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር፣ ቀጥታ ካልሆነ የታክስ 196 ሚሊየን ብር እና ታክስ ነክ ካልሆነ ገቢ 32 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 96 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በመቅረፍና አሰራሮችን በማዘመን የእቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉን አንስተዋል።
በቀጣይ የበጀት አመትም 964 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት ሃላፊዋ ÷ በክልሉ ለአንድ ወር የሚቆይ የቀን ገቢ ግምት መረጃ አሰባሰብ ንቅናቄ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ይህም የክልሉን ገቢ በአግባቡ ከመሰብሰብ እና ፍትሃዊ የታክስና የግብር ስርዓትን እንዲሰፍን ከማድረግ አንፃር እንዲሁም ወደ ንግድ እና ታክስ ስርዓቱ ያልገቡ ግብር ከፋዮችን ወደ ስርዓቱ በማስገባት የታክስ ስርዓትን ፍትሃዊና ታማኝነት ያለው እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ክልል አቀፉ የቀን ገቢ ግምት ውጤታማ እንዲሆን ተገቢውን መረጃ በመስጠትና ተባባሪ በመሆን የበኩሉን ከፍተኛ ድርሻ እንዲወጣ መጠየቃቸውን ከሀረሪ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version