አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘንድሮ ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የሚስችላቸውን ስራ ዛሬ በይፋ ጀምረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙዔል ኡርቃቶ ÷ በአዲስ አበባ ካሳንቺስ አካባቢ የሁለት አቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት ዛሬ አስጀምረዋል።
በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግርም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ስራ ከሆኑት ሶስት ዘርፎች አንዱ ማህበረሰቡን ማገልገል ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በዘንድሮ ክረምት ችግረኛ ወገኖችን በተለያዩ መንገዶች በመደገፍና የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች በመፍታት ጠንካራ ተሳትፎ እናደርጋለን ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከአርባ በሚልቁ ዩኒቨርስቲዎች ተግባራዊ እንደሚደረግና ፕሮግራሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚከናወንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ÷ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ ዜጋ ከማፍራት በተጓዳኝ ህብረተሰቡን ማገልገል ዋና ትኩረታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን በአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የምገባ ፕሮግራም ላይ ምግብ በማቅረብ እየተሳተፈ መሆኑን አስታውሰዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

