Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰኔ ወር ዋጋ ግሽበት 24 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳየ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰኔ ወር የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ24 ነጥብ 5 ከመቶ ጭማሬ አሳይቷል፡፡
የምግብ ዋጋ ግሽበት የሰኔ ወር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ28 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በዳቦና እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም የቀጠለ ሲሆን፥ በተለይ የበቆሎና የገብስ ዋጋ በፍጥነት ጨምሯል፡፡
በተጨማሪም ሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም፣ በርበሬና ቡና የዋጋ ጭማሪ በዚህም ወር በመቀጠላቸው ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ በፍጥነት መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ በያዝነው ወርም ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮል፣ ልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶና የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ ህክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡
አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ሰባት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ለኢፕድ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
Exit mobile version