አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሃገራት የምትሰጠው ችግኝ ቀጠናዊ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
አንድ ቢሊየን ችግኝ ደግሞ ለጎረቤት አገራት የሚሰጥ ሲሆን በዚህም ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ለመድረስ የታቀደ መሆኑም ይታወቃል።
የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ዛሬ በሱባ መናገሻ ደን አካባቢ የችግኝ ተከላ አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
ለግብርና፣ ለበቂ ውሃ አቅርቦት፣ ለብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ፣ ለስነ ምህዳር አገልግሎት፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለደን ውጤቶችና ለሌሎችም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጎረቤት አገራት የምታደርሰው ችግኝም ለቀጠናዊ ትብብር፣ ለልማት፣ በጋራ ለማደግ እና የጋራ መድረክ ለመፍጠር የራሱ አስተዋጽኦ አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጎረቤት አገራትን ትብብር የሚያጎለብት እና በሰላም አብሮ የመስራትን እድል የሚያጠናክር ነው ብለዋል ፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

