Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ ሱዳን ሊወጡ የነበሩ 51 ሰዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ ሱዳን ሊሻገሩ የነበሩ 51 ግለሰቦችን ትናንት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

የምእራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ጫኔ እንደገለጹት፥ ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ A3-32469 (አአ) በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ተይዘዋል።

ግለሰቦቹን ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ደላሎችና የአይሱዙ ረዳት ጨምሮ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የአይሱዙ አሽከርካሪው ለጊዜው በመሰወሩ ክትትል እየተደረበት መሆኑን አመልክተዋል።

አይሱዙ ተሽከርካሪው ሞተር ብስክሌት በሚያሽከረክሩ ሁለት ደላሎች መንገድ እየተመራ ይጓዝ እንደነበር የገለጹት ኃላፊዋ፥ የአይሱዙ አሽከርካሪውና ደላሎች በመካከላቸው የተፈጠረ አለመግባባት ለመያዛቸው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ ሱዳን ሊወጡ ከነበሩ 51 ሰዎች መካከልም 48ቱ ሴቶች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ግለሰቦቹ ለደላላና ለትራንስፖርት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ መክፈላቸውን ገልጸዋል።

እንደ ዋና ኢንስፔክተር ወርቄ ገለጻ፥ የተያዙት ሰዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version