አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉበትን ውስንነቶች በማቃናት ለቀጣዩ ፓርላማ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባው አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ጠቁመዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረክ የፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት፣ የጀንደር ኦዲት እንዲሁም የጥቆማ፣ ቅሬታና አቤቱታ አቀራረብ ስርዓትን ማዘመን ያስችላሉ የተባሉ የጥናት ሰነዶች ቀርበው በምክር ቤቱና በጽህፈት ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
አሁን ያሉት የምክር ቤት አባላት ለቀጣዩ ፓርላማ ልምዳቸውን የሚያጋሩበት መድረክ ቢመቻች፣ ምሁራንን በማማከር መስራት ቢቻል እንዲሁም የፓርላማ ዲፕሎማሲን በማጠናከር መንግስት የማይደርስባቸውን ቦታዎች ተደራሽ ለማድረግ ቢሰራ፤ የሚሉት ምክረ ሀሳቦች ከጥናቱ አቅራቢዎች የተሰነዘሩ ናቸው፡፡
ቋሚ ኮሚቴዎች ዝርዝር ነገሮችን ሳይሆን በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ባቀረቡት ጥናት የጠቆሙት ዶክተር ውብሸት፥ አባላቱ በበጀትም ሆነ በሰው ሀይል አስተዳደር ነጻ ሆነው መስራት እንደሚገባቸው ካቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ፓርላማው አስፈጻሚውን በመከታተልና የእርምት እርምጃ መውሰድ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ የጠቆሙት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፥ የጀንደር ኦዲትን በሚመለከት በፖሊሲ የተደገፈ አሰራር ሊኖር እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በፖርላማ ዲፕሎማሲ፣ በህግ አወጣጥ፣ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በውክልና ስራዎች ላይ የነበሩትን ውሱንነቶች መቅረፍ የሚያስችል አሰራር መከተል እንደሚገባና በመድረኩ የቀረቡትን ግብዓቶች ተጠቅመው ጥናቱን እንዲፈትሹ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለጥናቱ ባለሙያዎች ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም የቀረቡት የጥናት ሰነዶች ዳብረው ከተዘጋጁ በኋላ በቅርቡ ለሚመሰረተው ፓርላማ ግብዓት እንደሚሆኑ በነበረው መድረክ ላይ መጠቆሙን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

