አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በነገው እለት 351 ሚሊየን 735 ሺህ ችግኝ በዘመቻ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ማኖር መርሃግብር በክልል ደረጃ የሚከናወነውን ሥነሥርዓት በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ባለፉት ሶስት አመታት ችግኝ የመትከልና መንከባከብ ስራ እንደ ባህል እያደገ መምጣቱና በዘንድሮው አመት በክልል ደረጃ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ተነግሯል።
በአጠቃላይ በክልሉ ለዚሁ ዓላማ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በ GPS ተለይቶ መዘጋጀቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አማንቴ ገልፀዋል።
ቢሮው ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን በባሌ ተራሮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሠራው ስራ ከካርበን ሽያጭ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ በላይ ገቢ ተገኝቶ ህብረተሰቡ ከተገኘው ገቢ ተቋዷሽ መደረጉም በጋዜጣዊ መግለጫው ተነስቷል።
በዘንድሮው አመት ከ4 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን÷ እስከአሁን ድረስ 1ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኝ የተተከለ መሆኑ ተወስቷል።
በነገው እለት በኦሮሚያ ክልል በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ማኖር መርሃ-ግብር የ ኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል የሚያስፈልግ ጥንቃቄን ጨምሮ ለድንገተኛ አደጋ የመጀመሪያ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ከኦቢኤን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

